LELJOCH.COM
ጤና ይስጥልን! ድህረ ገጻችንን ለመጠቀም በመለያ መግባት አለቦት፡፡
በመለያ ለመግባት ወይንም አዲስ መለያ ለመፍጠር እስክሪኖ ላይ በስተግራ ጥግ ከፍ ብለው የሚታዩትን ሶስት ብርትኳናማ መስመሮች ይጫኑ!
በድሮ ዘመን ስምዒት ተብላ የምትጠራ እጅግ ዉብ
የሆነች ከተማ ነበረች፡፡ ይህች ከተማ ዉብ እና ጽዱ ከመሆኗ በተጨማሪ በሚያማምሩ የአበባ ቦታዎች እና ለምለም ሜዳዎች የተሞላች
ነች፡፡ የከተማዋ ነዋሪዎችም ደስተኞች እና ጤነኞች ስለነበሩ ከተማቸውን በደንብ ይንከባከቧት
ነበር፡፡
ስምዒት ከተማ በወፎች ዝማሬ፤ ከቦታ ቦታ በሚበሩ በባለ ብዙ ማራኪ ቀለም
ቢራቢሮዎች እና ማር ለመስራት አበቦችን በሚቀስሙ ንቦች ዘወትር እንዳማረባት ነች፡፡
አቤት የስምዒት ከተማ ማር ሲጣፍጥ!
በዛ ላይ ደግሞ በየሰዉ ግቢ
የንብ ቀፎ ስለተሰቀለ ማር እንደዉሃ በብዛት እና በርካሽ ይገኝ ነበር፡፡
በዚህች ከተማ ዉስጥ የሚኖር አቤል የሚባል ልጅ ነበር፡፡ አቤል እንደማንኛውም
የስምዒት ከተማ ልጅ ፍጹም ጤናማ ሲሆን በትርፍ ጊዜው በአበባ ስፍራ ተቀምጦ ማር እየላሰ ተረት ማንበብ በጣም ያስደስተዋል፡፡
ከእለታት አንድ ቀን እንደለመደው አቤል ለምለም ሜዳ መሃል የበቀለ ዛፍ ጥላ ስር ተቀምቶ የተረት መጽሃፉን እያነበበ ሳለ ከስሜት ህዋሳቶቹ አንዱ የሆነው አይን እንዲህ ሲል ተናገረ “ከስሜት ህዋሶች ሁሉ የምበልጠው እኔ ነኝ፡፡ እኔ ባልኖርኮ ይህንን ዉብ አለም ማየት አንችልም ነበር እንዲህ ደስ የሚል ተረትም ማንበብ አንችልም ነበር፡፡” ሲል እራሱን አሞካሸ፡፡
ይህንን የሰማው ጆሮም ላለመበለጥ በማሰብ “ከኔማ ፈጽሞ በጥቅም አትበልጥም! መስማት ከማየት በብዙ የተሻለ እና አስፈላጊ ችሎታ ነው! አስበው እስኪ የአእዋፋትን ዜማ እና የጓደኞችህን ድምጽ መስማት ሳትችል ስትቀር…” ሲል መለሰለት!
የአይን እና ጆሮ ንትርክ ከዚህ ጀምሮ እየባሰበት ሄደና ሁለቱም የሚሉትን
መሰማማት ትተው በከፍተኛ ድምጽ መጨቃጨቅ ጀመሩ፡፡
ይህን ጭቅጭቃቸውን የሰሙት ጓደኞቻቸው አፍንጫ፤ ምላስ እና እጅም ሊገላግሏቸው
በመሃል ገቡ፡፡
አፍንጫ ቀስ ብሎ በረዥሙ ከተነፈሰ በኋላ እንዲህ አላቸው፤
“እባካችሁ አይን እና ጆሮ አትጣሉ! ሁላችንምኮ የራሳችን የሆነ መናቅ የማይችል ጥቅም አለን፡፡ አቤል ጤናማ እና ደስተኛ እንዲሆን
እኩል ሃላፊነት ስላለብን ከመጣላት ይልቅ ተባብረን ብንሰራ ነው የሚሻለን፡፡”
ምላስም በመቀጠል “አዎን! እፍንጫ የተናገረው ትክክል ነው፡፡ አስቡት እስኪ እኔ ስራ አቁሜ አቤል የሚወደውን ማር ማጣጣም ሳይችል ቢቀር፣ ደስተኛ የሚሆን ይመሳላችኋል?”
እጅም በመስማማት “አንዳችን ካለ ሌላኛችን ድጋፍ አቤልን ደስተኛ አድርገን ለማቆየት በጣም እንቸገራለን፡፡ ስለዚህ እባካችሁ መጣላታችሁን ትታችሁ በመተባበር አብረን እንስራ!” አለ፡፡
ነገር ግን ከዚህ ሁሉ ምክር በኋላም አይን እና ጆሮ ከመታረቅ ፋንታ ጸባቸው
እየከረረ ንትርካቸውም እየባሰ ሄደ፡፡
በዚህም ተስፋ የቆረጡት አፍንጫ ምላስ እና እጅ አማራጭ ስላጡ አይን እና
ጆሮ እስኪታረቁ ድረስ የስራ አድማ ለማድረግ ወስነው ስራቸውን መስራት አቆሙ፡፡
አፍንጫ “ኣላሸትም”!
ምላስ “አልቀምስም”!
እጅም “አልዳስስም”!
ብለው ስራቸውን ሲያቋርጡ አቤል የሰውነቱ ድንገት ጤና ማጣት ግራ አጋባው፡፡
ሲልስ የነበረው ማር ከመሬት ተነስቶ ዉሃ ዉሃ ይለው ጀመር፤ የአበቦቹ ሽታ እና ሌላው የአካባቢዉ መአዛም ድንገት ጠፍቶ ሁሉም ነገር
ጠረን አልባ ሆነበት፡፡ እጁም መዳሰሱን ስላቆመ የሚነካው ነገር ሁሉ አንድ አይነት ሆኖበት ተቸገረ፡፡
በዚህም የተነሳ አቤል የስምዒት ከተማን ዉበት ማድነቅ ተስኖት በጣም ተቸገረ፡፡
እየቆየ ሲሄድም ከፍተኛ የሆነ ድብርት እና ጭንቀት ዉስጥ ገብቶ ከክፍሉ ሳይወጣ ብዙ ቀናት ቆየ፡፡
በአቤል ላይ ያደረሱትን ጉዳት የተመለከቱት አይን እና ጆሮም በተፈጠረው
ነገር ተጸጸቱ! ካለ አፍንጫ፤ ምላስ እና እጅ ብቃታቸው ሙሉ እንዳልሆነም ገባቸው፡፡ ስለዚህ በፍጥነት ወደ ጓደኞቻቸው ሄደው ይቅርታ መጠየቅ
ጀመሩ…
“እራስ ወዳድ ስለሆንኩ ከልቤ ይቅርታ እጠይቃለሁ!” አለ አይን በሰራው
ስራ ስላፈረ በጸጸት ድምጹን ዝቅ አድርጎ፡፡
ጆሮም በመስማማት እራሱን እየነቀነቀ “ከሁሉም የተሻልኩ ነኝ ብዬ ስፎካከር
ነበር! ነገር ግን አሁን ሁላችንም ለአቤል ጤነኝነት እንደምናስፈልግ ተረድቻለሁ!” አለ፡፡
አፍንጫ፤ ምላስ እና እጅም ይቅር አሏቸው እና ሁሉም ስራቸውን መስራት
ጀመሩ፡፡
አቤል ድንገት የጠፋበት ጤናው እንዲሁ ድንገት ስለተመለሰለት በጣም ደስተኛ
ሆነ፡፡ ከቀናት በኋላም ለመጀመሪያ ጊዜ ከክፍሉ ወጥቶ በለምለም ሜዳ ላይ ሲቦርቅ ዋለ፡፡
አምስቱ የስሜት ህዋሳትም በተናጥል ከመስራት ይልቅ ሲተባበሩ የተሻለ እንደሚሆኑ
ስለገባቸው ሁሉም ሃላፊነቱን በአግባቡ እየተወጣ በደስታ መኖር ጀመሩ፡፡