leljoch.com Logo

LELJOCH.COM

ጤና ይስጥልን! ድህረ ገጻችንን ለመጠቀም በመለያ መግባት አለቦት፡፡

በመለያ ለመግባት ወይንም አዲስ መለያ ለመፍጠር እስክሪኖ ላይ በስተግራ ጥግ ከፍ ብለው የሚታዩትን ሶስት ብርትኳናማ መስመሮች ይጫኑ!


የግላዊነት ፖሊሲ

ጥጃው ሳምሶን

በድሮ ዘመን በአንድ ሰፊ እና በአረንጓዴ ሳር በተሸፈነ ዙሪያው ደግሞ ጥቅጥቅ ባለ ጫካ የታጠረ ለምለም ሜዳ ላይ ከእናቱ ጋር በደስታ የሚኖር ሳምሶን የተባለ ጥጃ ነበር፡፡

 

የሳምሶን እናት እመት ብርሃኔ ሲሆን ስሟ ሳምሶንን ሁል ጊዜልጄ ሳምሶን፤ በፍጹም ከመንጋችን እንዳትለይ በተለይ ደግሞ ወደ ጥቅጥቁ ጫካ ዉስጥ ዘልቀህ እንዳትገባ! በጣም ብዙ እና አደገኛ አውሬዎች ስላሉ ይበሉሃል!” ስትል ታስጠነቅቀው ነበር፤

 

ጥጃው ሳምሶንም የእናቱን ምክር በመስማት ወደ ጥቅጥቁ ጫካ ዘልቆ ሳይገባ ኖረ፡፡

 

ከእለታት አንድ ቀን ግን ሳምሶን የምንጭ ዉሃ ለመጠጣት ወደ ጫካው ተጠግቶ ሳለ አንዲት የምታምር ቢራቢሮ ስትበር ያያል፡፡

 

የቢራቢሮዋ ውበት እጅግ ስለማረከው ጥጃው ሳምሶን ይዞ ሊያያት ፈልጎ ይከተላት ጀመር።

 

ቢራቢሮዋን እስከምሽት እየተከተለ ሲሮጥ ለካ ጥጃው ሳምሶን ሳያውቀው ጫካው ውስጥ በጣም ርቆ እና ዘልቆ ገብቷል።

 

ሳምሶን ቢራቢሮዋን ማባረሩን ተወት አድርጎ ዙሪያውን ሲያስተውል በፍጹም ወደ እናቱ እመት ብርሃኔ መመለሻ አቅጣጫውን ማወቅ ተሳነው፡፡

 

በዚህም ምክንያት ጥጃው ሳምሶን ብቻውን ጫካው ዉስጥ በታላቅ ፍርሃት ዉስጥ ሆኖ ወደ እናቱ የሚመለስበትን አቅጣጫ ለማወቅ ይንከራተት ጀመር፡፡

 

ነገር ግን መመለስ ሳይችል ቀኑ መምሸት ጀመረ፡፡ በዚህም ምክንያት በጣም የተጨነቀው ሳምሶን ከአንድ ግዙፍ ዛፍ ተጠግቶ ማልቀስ ጀመረ፡፡ እያለቀሰ ሳለም ድንገት እንደዚህ የሚል ድምጽ ሰማ፤

“ጠፍተህ ነው አይደል አንተ ልጅ?”

በዚህ ድንገተኛ ንግግር በጣም የደነገጠው ሳምሶን ድምጹ ከየት እንደመጣ ለማወቅ አካባቢውን ዞር ዞር ብሎ በፍርሃት እየቃኘ

“አ…አዎን ጠፍቼ ነው! ማን ልበል?” አለ!

በመቀጠለም ድምጹ እንዲህ አለው፤

አይዞህ አትፍራ! እኔ ጉጉቱ ኮኮ ነኝ! ቀና በል ዛፉ ላይ ሆኜ ነው የማወራህ!”

ይሄን ጊዜ ሳምሶን አንጋጦ የዛፉን ቅርንጫፍ ሲመለከት ኮኮን ከግዙፉ ዛፍ ቅርንጫፍ ላይ ሆኖ ቁልቁል ሲመለከተው አየው!

“ከየት ነው የመጣኸው!” ብሎ ኮኮ ሳምሶንን ሲጠይቀው ሳምሶን በጫካው መሃል ከሚገኘው ለምለም እና ሰፊ ሜዳ እንደሆነ መጣው ነገረው፡፡

ይሄኔም ጉጉቱ ኮኮ ቦታውን እንደሚያውቀውና ወደ እናቱ እንደሚያደርሰው ነግሮት ሳምሶን በምድር ኮኮ ደግሞ ከዛፍ ዛፍ እየበረረ አብረው መጓዝ ጀመሩ!

ትንሽ እንደተጓዙ ጉጉቱ ኮኮ ከርቀት የሚንቀሳቀስ ነገር ስላስተዋለ ዳንኤልን ቶሎ እንዲደበቅ ነገረው ሳምሶንም ሮጦ ከአንድ የወደቀ ዛፍ ጀርባ ተደበቀ፡፡

 

የሚንቀሳቀሰው ነገር እየቀረበ ሲመጣ ግን ጉጉቱ ኮኮ ነገሩ አውሬ ሳይሆን ዉድ ጓደኛው የሆነው አጋዘኑ ሔና መሆኑን ተረዳ! በዚህም ሳማሶንን ከተደበቀበት እንዲወጣ ነገረው እና ወደ ሔና ወስዶ አስተዋወቀው!

 

አጋዘኑ ሔናም ጫካውን እጅግ በጣም ስለሚያውቀው እና አቋራጭ መንገዶችን ስለሚያውቅ አብሯቸው በመጓዝ ሳምሶንን እናቱ እመት ብርሃኔ ዘንድ በደህና ለማድረስ ስላሰበ ለሶስት አብረው መጓዝ ጀመሩ፡፡

 

ነገር ግን ገና ጥቂት እንደተራመዱ ጉጉቱ ኮኮ በከፍተኛ ጩኸት “ሩጡ ሩጡ ነብር መጣ ሩጡ! አምልጡ!” አለ!

 

ይሄን ጊዜም አጋዘኑ ሔና ወደ ሳምሶን ዞረና “ተከተለኝ! ወደ ኋላ እንዳትቀር!” አለና በፊት ሲጓዙበት ከነበረው በተለየ አቅጣጫ በታላቅ ፍጥነት መሮጥ ጀመረ. . .ሳምሶንም በሙሉ አቅሙ እየሮጠ ተከተለው!

 

ሔና መጀመርያ ብዙ የወዳደቁ ዛፎች እና ግንዶች ባሉበት የጫካው ክፍል አንጣጥ እንጣጥ እያለ በታላቅ ፍጥነት ሮተ. . .

 

ቀጥሎ ደግሞ ቁልቁለታማ እና ትልልቅ ቋጥኞች ባሉበት ቦታ በተመሳሳይ ፍጥነት ሮጠ. . .

 

የሚሮጡበት ቦታ ሁሉ እጅግ ከባድ እና አስቸጋሪ ቢሆንም ሳምሶን ግን በተቻለው አቅም ከሔና ሳይርቅ ተከተለው. . .

 

በስተ መጨረሻም ከአንድ ሰፊ ሜዳ ደርሰው መሮጥ ጀመሩ. . .

 

እንዲሁ ፍጥነታቸውን ሳይቀንሱ በጣም ብዙ ከሮጡ በኋላ ከርቀት የጉጉቱ ኮኮ ድምጽ “በቃ አትሩጡ አምልጣቹታል! ቁሙ በቃ ቁሙ!” ሲላቸው ሰሙት!

 

ነገር ግን ገና እንደ ቆሙ ነበር ጥጃው ሳምሶን ያሉበት ሜዳ የሱ ቤት መሆኑን ያወቀው!

 

ወዲያውኑም መንጋውን ከርቀት ተመለከተ! ላሞች ተሰባስበው እናቱን እያጽኗኗት ነበር፡፡

እናቱ እመት ብርሃኔ ልጇን ስታየው በታላቅ ደስታ ቦረቀች፣ ጥጃው ሳምሶንም ምክሯን ስላልሰማ እና ራሱን አደጋ ላይ ስለጣለ አሷንም ስላስጨነቃት ከልቡ ይቅርታ ጠየቃት!

ቀጥሎም ህይወቱን ያተረፉትን ጉጉቱ ኮኮ እና አጋዘኑ ሔናን አስተዋውቋት እሷም ከልቧ አመሰገነቻቸው፡፡

 

ጥጃው ሳምሶንም ሁለት ምርጥ ጓደኞች እና ጥሩ የህይወት ትምህርት ተምሮበት ያጋጠመውን አደጋ አልፎ መኖር ቻለ!!


ተጨማሪ አዳዲስ ታሪኮች

አእምሮና ምናገባህ: Amharic tales for Children

ምናገባህ እና አእምሮ

የስሜት ህዋሳት ጸብ: Amharic tale

የስሜት ህዋሳት ጸብ

Ethiopian National Flag

የኢትዮጵያ ህዝቦች ብሄራዊ መዝሙር

Teaching about maps

ካርታ ምንድነው?

Water cycle (የውሃ ኡደት)

የውሃ ኡደት (Water cycle)

ዉቢት እና ጭራቁ: Amharic tales for children

ውቢት እና ጭራቁ

ሰባተኛው እና የመጨረሻው የሲንባድ ጉዞ: Amharic tales

ሰባተኛው እና የመጨረሻው የሲንባድ ጉዞ

ስድስተኛው የሲንባድ ጉዞ: Amharic tales

ስድስተኛው የሲንባድ ጉዞ

search

ተረት መፈለግያ