ስድስተኛው የሲንባድ ጉዞ
ከስድስተኛው ጉዞዬ ወደ ቤት ስመለስ እንደገና ወደ ባህር የመሄድ ሀሳቤን ሙሉ በሙሉ ትቼ ነበር። ምክንያቱም ዕድሜዬ በመግፋቱ እረፍት የምፈልግበት ጊዜ ከመሆኑ በተጨማሪ፣ ያጋጠሙኝን መሰል አደጋዎች ራሴን ድጋሚ ላለማጋለጥ ቆርጬ ነበር፤ ስለዚህም የቀረውን ዘመኔን በሰላም ከማሳለፍ በቀር ምንም አላሰብኩም። አንድ ቀን ግን የከሊፋው መኮንን ወደ እኔ መጥቶ ካሊፋው እንደላከው እና ሊያናግረኝ ስለሚፈልግ እንደጠራኝ ነገረኝ።
መልእክተኛውን ተከትዬ ቤተመንግሥት ከሄድክ በኋላ ከካሊፋው ፊት ሲያቀርቡኝ ከፊቱ ሰግጄ እጅ ነሳሁት።
"ሲንባድ, አገልግሎትህ ስላስፈለገኝ ነው ያስጠራውህ! ባለፈው ላመጣህልኝ ደብዳቤ መልስ ስላለኝ ለሰረንዲቡ ንጉስ እንድታደርስልኝ እፈልጋለሁ።" አለኝ!
የከሊፋው ትእዛዝ መብረቅ የመታኝ እስኪመስለኝ ነው ያደነዘዘኝ።
"ክቡርነትዎ; የእርሶን ትእዛዝ ለመፈጸም ምንም ነገር ለማድረግ ዝግጁ ነኝ ነገር ግን በጉዞዬ የደረሰብኝን አስበው ይሄንን ትእዛዞን ሌላ ሰው እንዲፈጽም ቢያደርጉ ደስ ይለኛል። በዛ ላይ ደግሞ ባግዳድን ድጋሚ ለቅቄ ላለመሄድ ምያለሁ።" አልኩ!
ነገር ግን የከሊፋውን እምቢተኝነት ስመለከት ትእዛዙን ልፈጽም ተስማማሁ። በዚህም እጅግ በጣም ተደሰተና ለጉዞዬ ይሆነኝ ዘንድ አንድ ሺህ አልማዞች ሰጠኝ።
በጥቂት ቀናት ውስጥ ለጉዞ ተሰናድቼ ጨረስኩ። የንጉሱ ደብዳቤ እና ስጦታዎች እንደደረሱኝ ወደ ቡሶራህ ተጓዝኩ እና ከዛም እጅግ በጣም ጉዞ አደረኩ። ወደ ሰረንዲብ ደሴት ስደርስም እስከ ቤተመንግሥቱ ድረስ ታላቅ አቀባበል ተደረገልኝ።
ንጉሱ ፊት ስደርስም መሬት ድረስ አጎንብሼ እጅ ነሳሁት።
"ሲንባድ" አለኝ ንጉሱ...
"እንኳን ደህና መጣህ! ስላንተ አብዝቼ አስብ ነበር; ድጋሚ የተገናኘንባት ቀን የተባረከች ትሁን!"
የካሊፋው ደብዳቤ እንደሚከተለው ነበር:
"በእውነተኛው እና ሉአላዊ አምላክ ከተመረጠው እና የነብዩ ምክትል መሪ አድርጎ በሾመው ሀሩን አል ረሺድ ስም ለተከበሩ የሰረንዲቡ ራጃ ታላቅ ሰላም ይሁን።
ደብዳቤዎትን በላቀ ደስታ ሆነን ተቀብለናል። መልስ ይሆንልን ዘንድም ከንጉሰ ነገስቱ ቤተመንግሥት ልከንሎታል። ሲደርሶት መልካም ሀሳባችን ገልጾ እንደሚያስደስቶት ባለሙሉ ተስፋ ነኝ።
አመሰግናለሁ !"
የከሊፋው ስጦታ ከወርቅ እና አንድ ሺህ አልማዞች የተሰራ ሙሉ ልብስ, ከውድ ነገሮች የተሰሩ ሀምሳ ልብሶች, በመቶዎች የሚቆጠሩ ከካይሮ, ሱዊዝ, እና አሌክሳንድሪያ የተገዙ ምርጥ ምርጥ ነጫጭ ልብሶች።
ከስጦታዎቹ ውስጥ አንዱ ከጥልቀቱ ስፋቱ የሚበልጥ ሶስት ሴንቲ ሜትር ውፍረት እና ግማሽ ሜትር ስፋት የሚበልጥ ለየት ካለ እና ባለብዙ ቀለማት ከሆነ እሳተ ገሞራ ከፈነዳበት ቦታ ብቻ ከሚገኝ አጋቴ ከሚባል ዲንጋይ የተሰራ ጎድጓዳ ሳህን ነበር። ሳህኑ ውስጡ ሲታይ ተንበርክኮ በቀስት አንበሳ የሚያድን ሰው አለ።
በተጨማሪም ከሊፋው የጠቢቡ ሰለሞን እንደነበር የሚወራለትን ውድ ጡብም ልኳል።
የሰረንዲቡ ንጉስም እጅጉን ተደሰተ።
ይህ ከሆነ ከጥቂጥ ጊዜ በኋላ ወደ ሀገሬ እንድመለስ እንዲፈቅዱልኝ ንጉሱን ጠይቄ በስንት መከራ ተፈቀደልኝ። ንጉሱ ሲሸኘኝ በጣም ብዙ ስጦታ ሰጠኝ። በፍጥነትም ወደ ባግዳድ ለመድረስ ተስፋ አድርጌ ለመመለስ ጉዞ ጀመርኩ። ነገር ግን የአምላክ ሀሳብ ሌላ ነበር...
ጉዞ በጀመርን በሶስተኛ ቀናችን በባህር ላይ ዘራፊዎች ጥቃድ ደረሰብን እና መርከባችን ለጦርነት የተሰራች ስላልነበረች በቀላሉ በቁጥጥር ስር አዋሉን። ዘራፊዎቹን ለመዋጋት የሞከሩ ጥቂት የመርከባችን ሰዎች ተገደሉ። እኔና ሌሎቻችን ምንም ስላልታገልን ዘራፊዎቹ ራቅ ወዳለ ደሴት ወሰዱን ሸጡን።
እኔን አንድ ሀብታም ነጋዴ ገዛኝ እና ወደ ቤቱ አምጥቶ በጥሩ ሁኔታ ተንከባከበኝ እንደ አገልጋይም ደህና ልብስ አለበሰኝ። ከጥቂት ቀናት በኋላም ምን መስራት እንደምችል ጠየቀኝ።
እኔም የእደጥበብ ሰው ሳልሆን ነጋዴ እንደሆነንኩ የሸጡኝ ነጋዴዎችም ንብረቴን ሁላ እንደዘረፉኝ ነገርኩት።
"ቀስት እና ደጋን መጠቀምስ ትችላለህ?" ብሎ ጠየቀኝ
ልጅ እያለሁ ቀስጥ እጠቀም እንደነበር ነገርኩት።
በመቀጠልም ደጋን እና ቀስት አስያዘኝ እና ከከተማው ርቆ ወደሚገኝ ጥቅጥቅ ጫካ በዝሆን ተጭነን ሄድን። ወደጫካው ውስጥ ጠልቀን ከገባን በኋላ አንድ ቦታ መርጦ አቆመ።
አንድ ረጅም ዛፍ ላይ ወጥቼ ዝሆኖች በዚህ ጫካ ውስጥ ብዙ ስላሉ በስር ሲያልፉ ጠብቄ እንድመታቸው ነገረኝ። አንዳቸውን መትቼ ከጣልኩም ያለበት መጥቼ እንዳሳውቀው ነግሮ ምግብ እና መጠጥ ሰጥቶኝ እዛው ዛፍ ላይ እንዳድር ጥሎኝ ሄደ።
አዳሩን ሙሉ ምንም አይነት ዝሆን አላየሁም ነበር። ሊነጋጋ ሲል ግን በጣም ብዙ ዝሆኖች ተመለከትኩ። በጣም ብዙ ቀስት ተኮስኩባቸው እና በስተመጨረሻ አንዱ ዝሆን ወደቀ። ሌሎቹ ዝሆኖች ገለል ሲሉልኝ ጠብቄ ከዛፉ ወረድኩና ለአለቃዬ ስኬቴን ልነግረው ሄድኩ።
እንደተሳካልኝ ስነግረው ብቃቴን እያደነቀ በጣም አደነቀኝ። ቀጥሎም አብረን ወደ ጫካው ሄድን እና ለዝሆኑ መቃብር ቆፍረን ቀበርነው። የአለቃዬ ሀሳብ ዝሆኑ ተቀብሮ ከበሰበሰ በኋላ ጥርሱን ነቅሎ ለመሸጥ ነበር።
ይህንን ስራ እየሰራሁ ለሁለት ወራት ቆየሁ።
አንድ ቀን ጠዋት ዝሆኖችን ዛፍ ላይ ሆኜ ስፈልግ እጅግ በሚገርም ሁኔታ ዝሆኖቹ እንደተለመደው በስሬ ከመለፍ ፋንታ በጣም በሀይለኛው እየጮሁ ወደ እኔ መጡ። ከብዛታቸውም የተነሳ መሬቱ ተሸፍኖ አካባቢው ሁሉ ይንቀጠቀጥ ነበር።
የተደበቅኩበትን ዛፍ ከበቡት እና ኩንቢያቸውን ወደ ላይ አድርጠው ሁሉም አፈጠጡብኝ። በጣም ከመደንገጤ የተነሳ ደንዝዤ ቀረሁ; ደጋን እና ቀስቶቼም ከእጄ አመለጡኝ።
መፍራቴ ትክክል ነበር! ምክንያቱም ዝሆኖቹ ካፈጠጡብኝ በኋላ ከመሀከላቸው ግዙፉ መጣና በኩምቢው ጠቅልሎ ዛፉን ያዘው። ከዛም ከስሩ ነቅሎ መሬት ጣለው። እኔም ከዛፉ ጋር አብሬ ወደቅኩ። ዝሆኑም ከወደቅኩበት በኩምቢው ጠቅልሎ አነሳኝና ጀርባው ላይ አስቀመጠኝ። ይሄ ሁሉ ሲሆን እኔ እንደ በድንጋጤ እንደ እሬሳ ደርቄ ነበር።
ቀጥሎ ዝሆኑ እኔን እንደጫነኝ ከፊት እየመራ ሌሎቹ እየተከተሉት በጣም ብዙ ርቀት ይዘውኝ ሄዱና ከጀርባው አወረደኝ እና ጥለውኝ ሄዱ።
ለጥቂት ጊዜ ከተኛሁ እና ዝሆኖቹ መሄዳቸውን ካረጋገጥኩ በኋላ ስነሳ እራሴን በረዥም እና ሰፊ ኮረብታ ላይ አገኘሁ። እንዳለ ዙሪያዬም በዝሆን ጥርስ እና አጥንተ ተሸፍኗል።
ያለሁበት ቦታ የዝሆኖች መካነ መቃብር መሆኑ ወዲያውኑ ገባኝ። ዝሆኖቹም ወደዚህ ቦታ ያመጡኝ የፈለግኩትን ያክል የዝሆን ጥርስ ከዚህ እንድወስድ እና እነሱን ከመጉዳት እንድታቀብ ለማሳወቅ ነበር። ኮረብታው ላይ ከመቆየት ይልክ ወደ ከተማ መጓዝ ጀመርኩ። አንድ ቀን እና አንድ ለሊት ተጉዤም አለቃዬ ያለበት ደረስኩ።
አለቃዬ እንዳየኝ "ውድ ሲንባድ, ምን ውስጥ ገባህ ብዬ በጣም ተጨንቄ ነበር። ወደ ጫካ ብሄድ የተነቀለ ዛፍ እና አጠገቡ ያንተ ቀስት እና ደጋንን ወድቆ አገኘሁ። ደግሜ የማይህም አልመሰለኝም ነበር። እባክህ ምን እንደገጠመህ ንገረኝ።" አለኝ
የገጠመኝን ሁሉ ነገርኩት እና በነጋታው ጠዋት ወደ ዝሆኖቹ መካነ መቃብር ተጓዝን። ይዞን የሄደውን ዝሆን የቻልነውን ያክል የዝሆን ጥርስ ከጫንነው በኋላ ወደ ቤታችን ተመለስን። ከዛም አለቃዬ ጠራኝ እና...
"ሲንባድ አንድ ነገር ልንገርህ። የጫካችን ዝሆኖች በየአመቱ ጥርስ ለማምጣት የላክናቸውን ብዙ ባሮች ሲገሉብን ኖረዋል። የፈለገ አይነት ዘዴ ብንጠቀምም ዝሆኖቹ ግን በፍጹም የሚሸወዱ አልነበሩም። ከቁጣቸው እንድንገላገል አምላክ አንተን መርጦ ልኮልናል። እኔንም ከተማችንንም ተዝቆ የማያልቅ ሀብት አጎናጽፈኸናል። ያውም ደግሞ ያለምንም አይነት ሞት የሚታፈስ ሀብት። ከዚህ በኋላ እንደ ወንድም እንጂ እንደ ባርያ ላይህ አልችልም። አምላክ በደስታ እና በብልጽግና ህይወትህን ይሙላው። ነጻነትህንም ከብዙ ሀብት ጋር መልሼ ሰጥቼሀለሁ።" አለኝ
ለዚህም እኔ "ጌታዬ አምላክ ያክብርልኝ! ነገር ግን እኔ ወደ ሀገሬ ከመመለስ ውጪ ከእርሶ ምንም አልፈልግም!" "ብዬ መለስኩለት።
"መልካም ሰሞኑን የዝሆን ጥርስ ለመውሰድ የሚመጡ መርከቦች ስላሉ ከነሱ በአንዲ ሸኝሀለሁ!" አለኝ
መርከቦቹ እስኪመጡ እየጠበቅኩ ከሱ ጋር ቆየሁ። በዚህ ጊዜም ወደ ዝሆኖቹ መካነ መቃብር ብዙ ጊዜ ተመላልሰን ያሉተንን መጋዘኖች ሁሉ በዝሆን ጥርስ ሞላናቸው። ሌሎቹ ነጋዴዎችም አለቃዬ ካጋጠመው መልካም እድል ስላካፈላቸው ተመሳሳይ አደረጉ።
በስተመጨረሻም መርከቦቹ መጡና አለቃዬ እራሱ የምጓዝበትን መርከብ መርጦልኝ ግማሹን በኔ ስም የዝሆን ጥርስ ጭኖ ሞላው። ለጉዞዬም የሚሆን ምግብ እና መጠጥ ጫነልኝ። በተጨማሪም በጣም ብዙ ስጦታዎች አምጥቶ እንድቀበለው አስገደደኝ። እጅግ በጣም አመስግኜው ስጨርስ ጉዞዬን ጀመርኩ።
ብዙ ደሴቶች ላይ አስፈላጊ ነገሮችን ለመሸማመት ቆምን። የኢንዲስን ወደብ ስንደርስ ወረድን። ወደ ቡሶራ በባህር መጓዝ ስላልፈለኩ የጫንኩትን የዝሆን ጥርስ አስወረድኩ። የዝሆን ጥርስ በመሸጥ በጣም ብዙ ማትረፍም ቻልኩ።
ዝግጅቴን ስጨርስ ከብዙ ነጋዴዎች ጋር በአንድነት ሆኜ ጉዞ ቀጠልኩ። መንገዱ ረዥም እና አድካሚ ቢሆንም የባህር አደጋ የሌለበት ስለሆነ ውስጤ ሰላም አጊኝቶ ተጓዝኩ።
ባግዳድ ስደርስም ከሊፋው ዘንድ ሄጄ ሀላፊነቴን መወጣቴን አሳወቅኩት። እሱሠፈም ብዙ ስጦታ ሰጥቶ አመሰገነኝ። ከዚያ ጊዜ ወዲህ እራሴን ለቤተሰቤ ለዘመድ አዝማድ እና ጓደኞቼ ሰጥቼ እየኖርኩ እገኛለሁ።
ሲንባድ በዚህ የሰባተኛው እና የመጨረሻው ጉዞውን ትርክት ከጨረሰ በኋላ ወደ ሂንባድ ዞሮ...
"እሺ ጓደኛዬ! እንደኔ የተሰቃየ ሰው በህይወትህ አጋጥሞህ ያውቃል? ከዚህ ሁሉ ስቃይ እና መከራ በኋላ የተረጋጋ እና ጥሩ ህይወት መኖር አይገባኝም!?" ብሎ ጠየቀው
ይሄን ጊዜም ሂንባድ እጁን እየሳመው...
"ጌታዬ! የኔ ችግር እና መከራ እርሶ ካሳለፉት ጋር ለንጽጽር ፈጽሞ መቅረብ የሚችል አይደለም። እርሶ ያሎት ሀብት እና ንብረት የምቾት ህይወትም ይገባዎታል። በዛ ላይ ደግሞ ሀብቶትን ለመልካም ነው የሚጠቀሙት። አምላክ ደስታ እና ከረዥም እድሜ ጋር ይስጦት።" አለው
በመቀጠልም ሲንባድ ሌላ መቶ አልማዞች እንዲሰጡት አዘዘና ሂንባድ የተሸካሚነት ህይወቱን ትቶ እንዲኖር እና ባሰኘው ጊዜም እየመጣ እሱ ቤት መመገብ እንደሚችል ለዛም ምክንያቱ ሲንባድ ተጓዡ የሚባል ጓደኛ ስላለው እንደሆነ ነገረው።