አምስተኛው የሲንባድ ጉዞ
ባለፉት አራት ጉዞዎቼ ያየሁት ስቃይ እና መከራ አሁንም አምስተኛ ዙር ከመጓዝ ሊያግደኝ አልቻለም። ስለዚህም ብዙ ሸቀጣሸቀጦች ገዝቼ ምርጥ ወደተባለ የወደብከተማ ተጓዝኩ እና ካፕቴን ከሚያዘኝ እራሴ የማዝበት የግሌ መርከብ እንዲኖረኝ ስለፈለኩ ከአንድ መርከብ አምራች ድርጅት ሄጄ የምፈልገውን አይነት መርከብ መርጬ እንዲሰሩልኝ አዘዝኩ እና እስኪዘጋጅልኝ እዛው ከተማ ቆየሁ።
መርከቡ ተሰርቶ ሲያልቅልኝ ሸቀጦቼን ይዤ ወደመርከቡ ወጣሁ። ነገር ግን የያዝኩት እቃ መርከቡን በጭራሽ ሊሞላው ስላልቻለ ሌሎች ነጋዴዎችንም ከነሸቀጣቸው ጫንኩ።
የባህሩ ነፋስ ለጉዞ ምቹ ሲሆን ጠብቀን ጉዞ ጀመርን እና በጣም ብዙ ተጓዝን። ከዛም ከአንድ ብቸኛ ደሴት ደርሰን ወርደን ስንጎበኝ የቀደመው ጉዞዬ ላይ ያጋጠመኝን ሮክ የተባለ እጅግ ግዙፍ ወፍ እንቁላል አገኘን። እንቁላሉ መፈልፈል እየጀመረ ኖሮ ማንቁርቱ ከቅርፊቱ ወጥቶ የሚታይ ጫጩት ሮክ ወፍ ውስጡ ነበር።
አብረውኝ የነበሩት ነጋዴዎች እንቁላሉን በገጀራ ሰብረው ቅርፊቱ ላይ ቀዳዳ ከሰሩ በኋላ ጫጩቱን ጎትተው አውጥተው ጠብሰውት ይበሉ ጀመር። ይሄን እንዳያደርጉና እንቁላሉን እንደነበር እንዲተውት ባስጠነቅቃቸውም ሊሰሙኝ ፍቃደኛ አልነበሩም።
ብዙም የጠበሱትን እንቁላል ሳይበሉ በድንገት ከርቀት አጅግ በጣም ግዙፍ ደመናዎች በሰማዩ ላይ ታዩ። የቀጠርኩት የመርከቤ አዛዥም ረዥም ልምድ ያለው ስለነበር ያየናቸው ሁለት ደመናዎች የተበላው እንቁላል እናት እና አባት መሆናቸውን እና ከመጣብን አደጋ ለማምለጥ በተቻለን አቅም ፈጥነን ወደመርከቡ እንድንመለስ ነገረን።
ሁለቱ ወፎች ደርሰው ልጃቸው መበላቱን ሲያዩ በአስፈሪ ሁኔታ እየጮሁ ትንሽ ሲያንዣብቡ ቆዩና በመጡበት አቅጣጫ ተመልሰው እየበረሩ ሄደው ለጥቂት ጊዜ ከአይናችን ተሰወሩ። ይህ ሁሉ ሲሆን እኛ የመጣብንን አደጋ ለማምለጥ በመርከባችን በፍጥነት እየተጓዝን ነበር።
ብዙም ሳይቆዩ ወፎቹ ተመልሰው መጡ, እግሮቻቸው ጥፍሮችም ግዙፍ ቋጥኝ ይዘው ነበር የተመለሱት። የመጀመርያው ወፍ ከመርከባችን አናት ትይዩ ሲደርስ የያዘውን ቋጥኝ ለቀቀብን; ሆኖም ግን በቀዛፊያችን ቀልጣፋነት ሸወድነው እና ግዙፍ ቋጥኝ ባህሩ ውስጥ ሊወድቅ ቻለ።
ሁለተኛውም ወፍ በተመሳሳይ ሁኔታ የያዘውን ቋጥኝ ሲለቅብን ቀዛፊአችን ሊሸውደው አልቻለም ነበር; ቋጥኙም የመርከቡ መሀል ላይ ስለወደቀ ብትንትን አደረገው።
መርከቡ ላይ የነበሩት ባህርተኞች ሁሉ ወይ ቋጥኙ ወድቆባቸው ካልሆነም ሰምጠው አለቁ። እኔም ከመርከቡ ጋር አብሬ ሰምጬ የነበረ ቢሆንም ተመልሼ ወደላይ ዋኘሁና አንድ የተንሳፈፈ ግንዲላ ይዤ ተረፍኩ።
በመቀጠልም በአንድ ይዤ እንጨቱን እንዳቀፍኩ በሌላኛው እጄ ስዋኝ ቆየሁ። ከዛም ነፋስ እና ማእበሉ ተባብረው ወደአንድ ደሴት ወሰዱኝ እና የባህር ዳርቻ ላይ ጣሉኝ።
ከድካሜ ለማገገም ሳር ላይ ተጋድሜ ትንሽ አረፍ አልኩና ስጨርስ ተነስቼ ደሴቱን እየተዘዋወርኩ መጎብኘት ጀመርኩ።
በጣም ጣፋጭ ፍሬዎች የተተከሉበት የአትክልት ቦታ ይመስላል።
በጣም የተለያዩ እና ጣፋጭ ፍሬዎችን ያፈሩ ዛፎች በየቦታው አገኘሁበት። ንጹህ እና የሚፍለቀለቅ የምንጭ ውሃም አገኘሁ። ከጣፋጮቹ ፍራፍሬዎች እስክጠግብ በልቼ ከምንጩ ውሃም ጠጣሁ።
ወደ ደሴቱ ውስጥ ዘልቄ ስገባ አንድ የደከመ እና ጥውልግ ያለ ሽማግሌ ሰውዬ ከወራጅ ውሃ አጠገብ ተቀምጦ ተመለከትኩ።
እንደኔ ከመርከብ ጋር ከመስመጥ የተረፈ ሰው ስለመሰለኝ ሄጄ ሰላም አልኩት።
ሰውዬው ግን ጭንቅላቱን በትንሽ ነቅንቆ ብቻ በቸልተኝነት ሰላም አለኝ። ስለምን ቆዝሞ እንደተቀመጠ ስጠይቀው ጥያቄዬን ከመመለስ ፋንታ በምልክት በጀርባዬ አዝዬ ወራጁን ውሃ እንዳሻግረው ጠየቀኝ።
እኔም ሽማግሌውን ሰውዬ ለመርዳት ምንም ሳላመነታ ከተቀመጠበት በጀርባዬ አዘልኩትና ወራጁን ውሃ አሳለፍኩት! ከዛም ቀስ ብሎ እንዲወርድ ስነግረው ያ ደካማ የነበረ ሽማግሌ ከየት እንዳመጣው በማላውቀው ፍጥነት, መተጣጠፍ እና ጉልበት ትከሻዬ ላይ ወጥቶ በጭኖቹ መሀል አንገቴን አደረገ።
ትከሻዬ ላይ እንደወጣ ጉሮሮዬን በጣም አንቆ ስለያዘኝ መተንፈስ ከበደኝ እና እራሴን ስቼ ወደቅኩ።
ከቆይታ በኋላ ወደራሴ ስመለስ እራሴን መሬት ወድቄ አገኘሁት። ሽማግሌው ሰውዬ ግን አሁንም ከትከሻዬ ሳይለይ መሬት ላይ ተኝቶ ነበር!
መንቃቴን እንዳየም በአንደኛው እግሩ ተረከዝ በሀይለኛው ጎኔን መታኝ, የዚህን ጊዜ ሳልፈልግ በግድ ዘልዬ ከወደኩበት ተነስቼ ቆምኩ።
ቀጥሎም በግድ ወደዛፎች ተሸክሜ እንድወስደው እያደረገኝ ፍራፍሬዎችን እየለቀመ መብላት ጀመረ። ቀኑን ሙሉ ከላዬ ላይ ሳይወርድ በግድ ወደሚፈልግበት እንድወስደው እያደረገኝ ይውላል። ማታም ስተኛ በጭኖቹ መሀል አንገቴን አድርጎ ጉሮሮዬን አጥብቆ ይዞኝ ያድራል።
ሁል ቀን ጠዋት በቁንጥጫ ከእንቅልፌ ይቀሰቅሰኝና በተረከዞቹ ደረቴን እየደበደበ ወደሚፈልግበት እንድወስደው ያደርገኝ ነበር።
አንድ ቀን ብዙ ከዛፍ ወድቀው የደረቁ ቅሎች አገኘሁ። ከዛም ከመሀላቸው ትልቁን መርጬ ወሰድኩና ውስጡን አጽድቼ ደሴቱ ላይ በብዛት የሚገኘውን ጣፋጭ የወይን ፍሬ ሞላሁበትና ከደንኩት።
ከዛም ቅሉን ደህና ቦታ ደብቄ ከቀናት ኋላ ተመልሼ መጥቼ ከፍቼ ብቀምሰው እጅግ በጣም ጣፋጭ ወደሆነ የወይን መጠጥነት ተቀይሮ አገኘሁት።
ከወይኑ ጥቂት ከተጎነጨሁ በኋላ በጣም ውስጤን ደስ ስላሰኘኝ እና ሀይል ስለሰጠኝ ሽማግሌውን እንደተሸከምኩት በደስታ መዝፈን እና መጨፈር ጀመርኩ።
ይህንን የተመለከተው ሽማግሌ ሰውዬ በምልክት ለሱም ከጠጣሁት የወይን መጠጥ እንድሰጠው ጠየቀኝ።
መጠጡን የያዘውን ቅል ሰጠሁት።
በጣም ስለጣፈጠው ቅሉ ውስጥ የነበረው ወይን ብዙ ቢሆንም ጭልጥ አድርጎ ጠጣው። ቀጥሎ እሱም እንደኔ መዝፈንና እላዬ ላይ እንደተቀመጠ መወዛወዝ ጀመረ።
በስካር መንፈስ ትከሻዬ ላይ ሆኖ ሲወዛወዝ በመዘናጋት አጥብቆ ይዞት የነበረውን ጉሮሮዬን ለቀቅ ሲያደርግልኝ ከላዬ ላይ ወርውሬ መሬት ጣልኩት። ሲወድቅ በሀይለኛው ስለነበር ከወደቀ በኋላ አልተንቀሳቀሰም; እኔም እዛው ጥዬው ሸሽቼ ከቦታው ሄድኩ።
ከዛ ጨካኝ ሽማግሌ ስላመለጥኩ ደስ እያለኝ ወደ ባህሩ ዳርቻ ሄድኩ። እንደመታደል ሆኖም የአንድ መርከብ ሰዎች የሚጠጣ ውሃ ለመቅዳት ከባህሩ ዳርቻ ከነመርከባቸው ቆመው አገኘኋቸው።
ሲያዩኝ ተገረሙ; ታሪኬን የገጠሐኝን ስነግራቸው ደግሞ ይበልጡኑ ተደመሙ።
"ከሽማግሌው ሰውዬ እጅ አመለጥክ?" አሉኝ!
"ከሱ ሰውዬ እጅኮ ማንም አምልጦ አያውቅም; የያዛቸውን ሰዎች እስኪሞቱ ድረስ ከላያቸው አይወርድም። ሲያስቸግሩትም በጣም ብዙ ሰዎችን አንቆ ገሏል! ከሱ እጅ ስታመልጥ አንተ የመጀመርያው ሰው ነህ!" አሉኝ።
በመቀጠል ሰዎቹ ወደካፕቴናቸው ይዘውኝ ሄዱ; እሱም በጥሩ እንክብካቤ ተቀበለኝና የባህር ጉዞ ጀመርን። ከጥቂት ቀናት ጉዞ በኋላ ከአንድ የባህር ዳርቻ ላይ የተመሰረተች ከተማ ደረስን። የከተዋ ቤቶች አሰራር ከባህሩ ላይ የተንሳፈፉ አስመስሏቸው ነበር።
በመርከብ ላይ ያፈራሁት አንድ ጓደኛ ነበረኝ። አዚች ከተማ ስንደርስ ይህ ጓደኛዬ ከኮኮናት ለቃሚዎች ጋር አስተዋወቀኝ በኋላ ባዶ ጆንያ ሰጥቶ አብሪአቸው እንድሄድ መከረኝ።
"አብረሃቸው ሂድ የሚያደርጉትን ሁሉ ነገርም አድርግ, ነገር ግን በፍጹም ከነሱ እንዳትለይ አለበለዚያ አደጋ ላይ ልትወድቅ ትችላለህ!" አለኝ።
በመቀጠልም የምበላው እና የምጠጣው ሰጥቶ ሸኘኝ።
ከሰዎቹ ጋር ተጉዘን ጥቅጥቅ ያለ የኮኮነት ዛፎች ወደሞሉበት ደን ደረስን። ዛፎቹ በጣም ግዙፍ, ረጅም እና ልሙጥ ስለነበሩ ፍሬዎቹ ወዳሉበት መውጣት የማይታሰብ ነው።
ወደጫካው ስንገባ ብዙ ዝንጀሮዎች ተመልክተውን ሲሸሹ እና በሚያስገርም ፍጥነት የኮኮነት ዛፎቹን ሲወጡ ተመለከትን።
አብረውኝ የነበሩት ኮኮነት ለቃሚዎች ዲንጋይ እያነሱ ዝንጀሮዎቹ ላይ መወርወር ጀመሩ; እኔም አብሬአቸው ወረወርኩ። ዝንጀሮዎቹም በጣም ተናደው አጸፋውን ለመመለስ የኮኮናት ፍሬ እየበጠሱ ይወረውሩብን ጀመር።
ያንን ዘዴ ተጠቅመን በጣም ብዙ የኮኮናት ፍሬ መሰብሰብ ቻልን። እኔም የያዝኩትን ጆንያ ሞልቼ ጥሩ ትርፍ የሚያስገኝ ስራ መስራት ቻልኩ።
መርከባችን ላይ ኮኮናታችንን ከጫንን በኋላ የመርከብ ጉዞአችንን ቀጠልን። ከዛም የበርበሬ ቃርያ በጣም በብዛት የሚበቅልበት ደሴት ደረስን። ከዛ ቀጥለንም ምርጥ የእንጨት ዘር እና የአሎ ቬራ አትክልት ወደሚገኝባት የኮማሪ ደሴት ደረስን።
በለቀምኩት ኮኮናት ከነዚህ ሁለት ደሴቶች የበርበሬ ቃርያ, እንጨት እና አሎ ቬራ ገዝቼ ከሌሎች ነጋዴዎች ጋር ከባህር ውስጥ እንቁ ለቀማ ሄድኩ። እዛም ጠልቀው የሚዋኙ ሰዎች ቀጥሬ ትላልቅ እና ጥራት ያላቸው እንቁዎች አስለቀምኩ።
ከዛም የመርከብ ጉዞአችንን ቀጥለን ወደ ቡሶራ ሄድን እና በመቀጠል ወደ ባግዳድ መጣን።
እዚህ እንደደረስኩም ያመጣሁትን የበርበሬ ቃርያ እንጨት እና አሎ ቬራ ሸጬ ጥሩ ትርፍ አገኘሁ። ከቀደሙት ጉዞዎቼ ስመለስ እንዳደረኩትም የትርፌን አንድ አስረኛ ለተቸገሩ መጽዋት ሰጥቼ ከድካሜ ማረፍ ጀመርኩ።
ሲንባድ መቶ አልማዞች ለሂንባድ እንዲሰጠው አዘዘና ሂንባድ እና ሌሎቹም እንግዶቹ ነገ መጥተው የስድስተኛውን ጉዞውን ታሪክ እንዲሰሙት ጋበዛቸው።
ቀጣይ፡ ስድስተኛው የሲንባድ ጉዞ