leljoch.com Logo

LELJOCH.COM

ጤና ይስጥልን! ድህረ ገጻችንን ለመጠቀም በመለያ መግባት አለቦት፡፡

በመለያ ለመግባት ወይንም አዲስ መለያ ለመፍጠር እስክሪኖ ላይ በስተግራ ጥግ ከፍ ብለው የሚታዩትን ሶስት ብርትኳናማ መስመሮች ይጫኑ!


የግላዊነት ፖሊሲ

አራተኛው የሲንባድ ጉዞ


ቀዳሚ ክፍል፡ ሶስተኛው የሂንባድ ጉዞ


ከሶስተኛው ጉዞዬ አረፍ ካልኩ እና ካገገምኩ በኋላ የንግድ እና የጉዞ ፍቅሬ እንደ አዲስ አገረሸብኝ!

ስለዚህም ለጉዞ ያስፈልጉኛል ያልኳቸውን ነገሮች ሁሉ ሸማምቼ እና ጉዳዬን ጨርሼ ለጉዞ ተሰናዳሁ። ወደ ፐርዢያ ተጉዤ ብዙ ግዛቶችን ካዳረስኩ በኋላ ጉዞዬን ለመጀመር ወደ ወደብ መጣሁ። 

ገና ጉዞ በጀመርን ጥቂት ቀናችን ከፍተኛ ማእበል ስላጋጠመን ካፕቴናችን የመርከቧን ሸራ አውርዶ የመጣብንን አደጋ እንድናልፍ ለማድረግ ጣረ። 


ሆኖም ግን ልፋቱ ሁሉ በከንቱ ነበር! 


የመርከባችን ሸራ እና የሸራ መወጠርያ እንጨቶች ብትንትናቸው ወጣ; ብዙ ተጓዦች ሰመጡ; ጭነታችን ጠፋ; መርከባችንም አውላላ ባህር ላይ ተሰባብራ ቀረች!


እኔ ግን እድል ቀንቶኝ ከብዙ ነጋዴዎች እና የባህር ሰዎች ጋር ታንኳ አጊኝቼ መትረፍ ቻልኩ። በባህሩወጀብ ተገፍተን ቅርብ ወደምትገኝ አንዲት ደሴት ስለሄድን እዛ ሂይወታችንን ያተረፉልን ፍራፍሬዎች እና የሚጠጣ የምንጭ ውሃ ማግኘት ቻልን!

ታንኳችን ወስዳ ከጣለችን ቦታ ሆነንም ምሽቱን አሳለፍን።


በሚቀጥለው ቀን ጠዋት ጸሀይ እንደወጣች ደሴቲቱን እየተዘዋወርን ተመለከትን። ከርቀት ቤቶች ስላየን ወደ ቤቶቹ ተጉዘን ገና ከመድረሳችን በድንገት በብዙ ጥቋቁር ሰዎች ተከበብን።


ጥቋቁሮቹ ሰዎች ቆጥረው ከተከፋፈሉን በኋላ በየፊናቸው ይዘውን ሄዱ። እኔና አምስት ጓዶቼንም ይዘውን ወደ አንድ ቦታ ወሰዱን።


ወደ ቦታው እንደደረስን ካስቀመጡን በኋላ በምልክት እንድንበላ እየነገሩን የሆነ እጽዋት ሰጡን። ጓዶቼ ጥቁሮቹ እጽዋቱን አለመመገባቸውን ልብ ሳይሉ ረሀባቸውን ለማስታገስ በመስገብገብ የተሰጣቸውን ተመገቡ። እኔ ግን ጥርጣሬ ስላደረብኝ እንኳን ልበላው ልቀምሰው እንኳን አልፈቀድኩም!


ይሄም ውሳኔዬ በጣም እንደጠቀመኝ የገባኝ ጓዶቼ ከቁጥጥር ውጪ መሆናቸውን እና ሲያወሩኝ እንኳ ምን እያሉኝ እንደሆነ ሳያውቁ እንዲሁ ሲቀባጥሩ ስመለከት ነው።


በመቀጠልም ጥቋቁሮቹ ሰዎች በኮኮናት ዘይትየተሰራ ሩዝ አቀረቡልን, ከራሳቸው ጋር ያልነበሩት ጓዶቼ አሁንም በታላቅ መንገብገብ በሉት, እኔም በጣም ትንሽ ትንሽ በላሁ።


መጀመርያ እጽዋቱን የሰጡን ከበላነው በኋላ አቅላችንን እንድንስት ነበር...በመቀጠል ደግሞ ሩዙን የሰጡን ሰው በላዎች ስለነበረሩ ሊበሉን ፈልገው እንድንወፍርላቸው ነበር። ሀሳባቸውም ስለተሳካላቸው በየቀኑ ጓዶቼ እየወፈሩላቸው ስለሄዱ በተራ በተራ ይበሏቸው ጀመር።


እኔ ግን ብዙም ስለማልመገብ በየቀኑ ከመወፈር ፋንታ ይብሱኑ እየከሳሁ መጣሁ። የሞት ፍርሃት የሚቀርብልኝን ምግብ ሁሉ መርዝ መስሎ እንዲታየኝ አደረገብኝ። 


ይሄም ወደ ህመም ስለተቀየረብኝ ጓዶቼን ሁሉ በተራ በተራ የተመገቡት ጥቋቁር ሰዎች እኔን ግን ከመብላት ተቆጠቡ።


በዚህም ምክንያት ብዙ ነጻነት ይሰጡኝ ጀመር; ለማደርገውም ሆነ ለምሆነው ነገርም ግድ አጡ።


ይህንንም እንደአጋጣሚ በመጠቀም ከእለታት አንድ ቀን ቀስ እያልኩ በማዘናጋት ለማምለጥ አስቤ ቀስ እያልኩ ከቤቶቹ ርቄ ሄድኩ! ይህንን ሀሳቤን የተረዳ አንድ ሽማግሌ እንድመለስ ጮክ ብሎ ቢጠራኝም እንደማይደርስብኝ እና ሌላ ሰው እንደሌለ አይቼ እርምጃዬን በመጨመር ፈጥኜ ከቦታው ተሰወርኩ። 


የመንደሩ ነዋሪዎች ቀን ወጥተው ማታ መመለስ ልማዳቸው ስለነበር ይህ ለኔ ምቹ አጋጣሚ ሆነልኝ። እንደማይደርሱብኝም ስላወኩ ለሊቱን ሙሉ ያለማቋረጥ ተጓዝኩ። አልፎ አልፎ ከያዝኩት ምግብ ለመቅመስ ትንሽ ብቆምም ወዲያውኑ ግን ጉዞዬን እቀጥል ነበረ።

እንደዚህ እያደረኩ ሰው ያለባቸው የመሰሉኝን ቦታዎች እየሸሸሁ ተጓዝኩ።በጉዞዬም አብዛኛው ጊዜ የምመገበው ኮኮነት ነበር; ፈሳሹ መጠጥ ፍሬው ደግሞ ምግብ ስለሆነኝ በጣም ጠቅሞኝ ነበር።


በስምንተኛው ቀን ወደ ባህሩ አጠገብ ስደርስ ብዙ ሰዎች ተሰባስበው በደሴቱ ላይ በብዛት በቅሎ የሚገኘውን ቃሪያ ሲለቅሙ አገኘኋቸው!


ሰዎቹ ጥቋቁሮቹ አለመሆናቸውን እና ይልቁኑ እንደኔ ያሉ አረባውያን መሆናቸውን ስመለከት እጅጉን ደስ አለኝ።


ሰዎቹም እንዳዩኝ ወደኔ መጥተው ማንነቴን እና ከየት እንደምመጣ ጠየቁኝ። በቋንቋዬ ሲናገሩ ስለሰማኋቸው እጅግ በጣም ደስ ብሎኝ ሙሉ ታሪኬን ነገርኳቸው!


"እነዛ ጥቋቁር ሰዎችኮ ሰው በላ አውሬዎች ናቸው; እንዴት አድርገህ ልታመልጣቸው ቻልክ?" ብለው በመገረም ጠየቁኝ!


እኔም ነብሴን ለማትረፍ የተጠቀምኩትን ብልሀት ነግሬ አስደመምኳቸው!


ቃሪያቸውን ለቅመው እስኪጨርሱ ጠበቅኳቸው እና በመርከብ አብሪአቸው ወደመጡበት ደሴት ተጓዝኩ። ስንደርስ ወደ ንጉሳቸው አቀረቡኝ እና ቁጭ ብሎ ታሪኬን በታላቅ በገረም አዳመጠኝ። 

በመቀጠልም ይህ ንጉሳቸው እጅግ በጣም መልካም ስለነበር የምለብሰው ሰጥቶኝ አሽከሮቹ እንዲንከባከቡኝ አዘዛቸው።

ደሴቱ ብዙ ሰው ያለበት,  ሁሉም ነገር ሞልቶ የትረፈረፈበት እና ብዙ ንግድ የሚከናወንበት ታላቅ ከተማ ነበር። 

ካጋጠመኝ አደጋ ማምለጤ ሳያንስ በእንደዚህ ያለ ምቹ ከተማ መገኘቴ እጅጉን ተመቸኝ! በዛ ላይ ደግሞ የንጉሱ እንክብካቤ እርካታዬን ሙሉ አደረገው።

በአጭሩ ንጉሱ ከኔ በላይ የሚያቀርበው ሰው አልነበረም። በዚህም ምክንያት በከተማው ህዝብ ዘንድ ሁሉ ታዋቂ ሆንኩ, ከመጤ ይልቅም እንደከተማዋ ነባር ነዋሪ ተደርጌ መታየት ጀመርኩ።


የደሴቷ ነዋሪዎች ፈረስ ሲጋልቡ ልጓምም ሆነ ኮርቻ አይጠቀሙም ነበር! ይህንን ተመልክቼም ወደ አንድ ሰራተኛ ሄድኩና የራሴን ንድፍ ሰርቼ እንዲሰራልኝ ሰጠሁት። ሰርቶ ሲጨርስልኝም እራሴ በሌዘር እና በወርቅ ልጥፍ አሳምሬው በመቀጠልም ወደ ቀጥቃጭ ሄጄ መርገጫ በራሴ ንድፍ እንዲሰራልኝ አደረኩት።


ሁሉን ነገር ሰርቼ ስጨርስ ለንጉሱ በስጦታ መልክ አቀረብኩለት። በስጦታው እጅግ በጣም ስለተደሰተ ብዙ ስጦታዎች በማበርከት ምስጋናውን ገለጸልኝ። ለብዙ ሚኒስትሮቹና ተዛዥ አለቆቹም ሰራሁላቸው። በዚህም በጣም ታላቅ ተወዳጅነትን እና ከበሬታን አተረፍኩ።

በቋሚነትም ንጉሱን እጎበኘው ነበር። 

አንድ ቀን ንጉሱ እንደዚህ አለኝ...


"ውድ ሲንባድ! ከልብ ወዳጄ ሆነሀል ቀረቤታችንም እጅጉኑ የምደሰትበት ነው። ነገር ግን እምቢ እንድትለኝ የማልፈቅደው አንድ ነገር ላስቸግርህ። እሱም ወደ ሀገርህ ስለመመለስ ማሰብን ትተህ እዚሁ አግብተህ እንድትቀር ነው።" 


የንጉሱን ፍላጎት መጋፋት አልፈለኩም። በመሆኑም አንዲት ቆንጆ ሀብታም እና ከተከበረ ቤተሰብ የመጣች ሚስት መርጦ ዳረኝ። ከሰርጋችን በኋላ ለጥቂት ጊዜ ከሚስቴ ጋር በጥሩ ደስታ እና መስማማት ኖርኩ። ሆኖም ግን ከራሴ ይልቅ የንጉሱን ፍላጎት ስለነበረ እኖር የነበረው ውስጤ ደስተኛ አልሆንልህ አለኝ። ስለዚህም ባገኘሁት የመጀመርያ እጋጣሚ ጠፍቼ ወደ ናፈቀችኝ ሀገሬ ባግዳድ ለመመለስ ወሰንኩ።


ይህ በእንዲህ እንዳለ አንድ ጥሩ ቀረቤታ የነበረን ጎረቤቴ ሚስቱ በጠና ታማ ቆይታ ነበር እና ሞተች። እኔም ላጽናናው እና ከጎኑ ሆኜ ላበረታው ቤቱ ብሄድ በከባድ ሀዘን እና ትካዜ ተውጦ አገኘሁት።


ገና እንዳየሁትም እጅጉን ስላሳዘነኝ "አምላክ ያጽናህ ረጅም እድሜም ያጎናጽፍህ!" ብዬ ላጽናናው ሞከርኩ።


"ተወኝ እስኪ!" አለኝ ሀዘን ውስጥ እንዳለ...

"እንዴት ብዬ ነው ረጅም እድሜ የምጎናጸፈው? ዛሬ ከሚስቴ ጋር ልቀበር አይደል እንዴ? የቀረኝኮ አንድ ሰአት ብቻ ነው!" አለኝ።


ለካ ይሄ የደሴቱ ሰዎች ህግ ነው። ሚስቱ የሞተችበት ባል አብሯት ይቀበራል; ባሏ የሞተባት ሚስትም እንደዛው አብራው ትቀበራለች።


ይሄንን ዘግናኝ እና አስፈሪ ልምድ እያብራራልኝ ሳለ ዘመድ አዝማዶቹ እና ጓደኞቹ ለቀብር ስነስርአት መጡ። የሚስትየውን እሬሳ ውድ ውድ የሆኑ ልብሶቿን እና ጌጣጌጦቿን ሁሉ አልብሰው ለቀብሯ ሳይሆን ለሰርጓ የምትዘጋጅ አስመስለው ገነዟት። በመቀጠልም ክፍት በሆነ የሬሳ ሳጥን ጭነው ቀብሩ ወደሚፈጸምበት ከፍ ያለ ተራራ ተጓዙ።


እንደደረሱም የአንድን ጥልቅ ጉድጓድ ከድኖ የተቀመጠን ግዙፍ ዲንጋይ አነሱና ከነሙሉ ጌጡ እና አልባሳቱ የሴትየዋን እሬሳ ወደጉድጓዱ አስገቡት። በመቀጠልም ባልየው ወዳጅ ዘመዶቹን በየተራ እያቀፈ ከተሰናበተ በኋላ በሌላ የሬሳ ሳጥን እራሱ ገብቶ እሱንም ወደ ጉድጓዱ አወረዱት። ሰባት ሙልሙል እና አንድ ገንቦ ውሃ በሳጥኑ ውስጥ ተደርጎለት ነበር። እንዳወረዱትም ጉድጓዱን መልሰው በግዙፉ ዲንጋይ ዘጉት።


በዚህም የቀብር ስነስርዓቱ ስለተፈጸመ ቀባሪው ህዝብ ወደመጣበት ተመለሰ።


ይህንን የቀብር ስነስርዓት እንደዚህ አብራርቼ የነገርኳችሁ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ የኔም እጣ ፈንታ ስለሚሆን ነው። ሚስቴ ታመመች እና ሞተች! 


ለንጉሱ ያለ የሌለ ምክንያት እየደረደርኩ እና ለሀገሩም መጤ መሆኔን ተናግሬ ከዚህ ነገር እንዲታደገኝ ብማጸነውም ትርፉ ልፋት ሆነብኝ። የተለያዩ ከፍተኛ ባለስልጣናት እና የተከበሩ ሰዎች ስነስርዓቱ ላይ በመገኘት በጥሩ ክብር እንደሚቀብሩኝ በመናገር ሊያጽናኑኝ ሞከሩ።


የቀብሩ መጠናቀቂያ ላይም እንደጎረቤቴ አንድ ገንቦ ውሃ እና ሰባት ሙልሙል ዳቦ ጋር ወደ ጉድጓዱ ወረድኩ እና ተከደነብኝ።


ወደ ጉድጓዱ መጨረሻ ስደርስ ከላይ በሚገባ የብርሃን ጭላንጭል የቦታውን ተፈጥሮ ለመረዳት ሞከርኩ; መጨረሻ የሌለው ዋሻ ሆኖም አገኘሁት።


ዳቦና ውሃዬን ተጠቅሜ ለጥቂት ጊዜ መኖር ቻልኩ። የሆነ ቀን ግን አንድ የሚተነፍስ እና የሚንቀሳቀስ ነገር ከአጠገቤ ተሰማኝ። ወደ ድምጹ አየተንፏቀቅኩ ተጠጋሁ! ነገር ግን በደረስኩት ቁጥር እንስሳው ይሸሸኝ እና ይቆም ነበር። ለረዥም ግዜ ስጠጋው እና ሲሸሸኝ ከቆየን በኋላ በስተመጨረሻ ከርቀት የብርሃን ጭላንጭል ታየኝ። 


የታየኝ ብርሃን በጣም ሩቅ ስለነበር ትንሽዬ እና ሊጠፋ የደረሰ ኮከብ ነበር የሚመስለው። ብርሃኑ አንዳንዴ ከእይታዬ ቢጠፋብኝም መልሼ እንደምንም እያገኘሁት ወደሱ ጉዞዬን ቀጠልኩ። በስተመጨረሻም ደረስኩበት እና በተሰነጠቀ ዲንጋይ ውስጥ የሚገባ ብርሃን ሆኖ አገኘሁት።


በዲንጋዩ ስንጥቅ ውስጥ ሾልኬ ስወጣ እራሴን ከባህር ዳርቻ አገኘሁ። በዚህም እጅግ በጣም ደስተኛ ሆንኩ በባህሩ አሸዋ ላይም እየሰገድኩ አምላኬ ስላደረገልኝ ምህረት አመሰገንኩት። 

ብዙም ሳይቆይም እኔ በነበርኩበት ቦታ አንድ መርከብ ሲያልፍ ተመለከትኩ; በፍጥነት ጥምጣሜን ፈትቼ እያውለበለብኩ እና በታላቅ ድምጽ እየጮህኩ እንዲያዩኝ አደረኩና ጀልባ ልከው ወደ መርከቡ እንድወሰድ አደረጉኝ።


እድሌም ሆኖ ያገኙኝ ሰዎች የወጣሁበትን ቦታ ሳይመረምሩ እና ጥያቄ ሳያበዙ ወሰዱኝ።


ብዙ ደሴቶችን አልፈን ተጓዝን ከነዚህም ውስጥ ከሰሬንዲብ የአስር ቀን; ከኬላ ደግሞ የስድስት ቀን ጉዞ ርቀት ላይ የሚገኘው የቤልስ ደሴት አንዱ ነበር። ደሴቱ ላይ የሊድ ማእድን ማውጫዎች እና የህንድ ሸንኮራ በብዛት አሉ።


የኬላ ደሴት ንጉስ እጅግ በጣም ሀይለኛ እና ሀብታም ሲሆን የቤልስ ደሴትም ግዛቱ ነው። ነዋሪዎቹ እጅግ ኋላ ቀር ከመሆናቸው የተነሳ የሰው ስጋ ይመገቡ ነበር። 


በዛ ደሴት ላይ ጉዳያችንን እንደጨረስን የባህር ጉዞአችንን ቀጠልን እና ብዙ ወደቦችን ነካን; በመጨረሻም በደስታ ባግዳድ ደረስን። ከዘመድ አዝማድ ጋርም መገናኘት ቻልኩ። አምላክ ላደረገልኝ ነገር ምስጋና ይሆን ዘንድም ብዙ መስጊዶችን እና ድሆችን ረዳሁ።


በመቀጠልም ሲንባድ ሌላ የመቶ አልማዞች ስጦታ ለሂንባድ አበርክቶለት በማግስቱ በተመሳሳይ ሰአት እንዲመጣ እና እራት በልቶ የአምስተኛ ጉዞውን ታሪክ እንዲሰማ ጋብዞ አሰናበተው።


ቀጣይ ክፍል፡ አምስተኛው የሲንባድ ጉዞ


ተጨማሪ አዳዲስ ታሪኮች

አእምሮና ምናገባህ: Amharic tales for Children

ምናገባህ እና አእምሮ

ጥጃው ሳምሶን: Amahric story for children

ጥጃው ሳምሶን

የስሜት ህዋሳት ጸብ: Amharic tale

የስሜት ህዋሳት ጸብ

Ethiopian National Flag

የኢትዮጵያ ህዝቦች ብሄራዊ መዝሙር

Teaching about maps

ካርታ ምንድነው?

Water cycle (የውሃ ኡደት)

የውሃ ኡደት (Water cycle)

ዉቢት እና ጭራቁ: Amharic tales for children

ውቢት እና ጭራቁ

ሰባተኛው እና የመጨረሻው የሲንባድ ጉዞ: Amharic tales

ሰባተኛው እና የመጨረሻው የሲንባድ ጉዞ

search

ተረት መፈለግያ