leljoch.com Logo

LELJOCH.COM

ጤና ይስጥልን! ድህረ ገጻችንን ለመጠቀም በመለያ መግባት አለቦት፡፡

በመለያ ለመግባት ወይንም አዲስ መለያ ለመፍጠር እስክሪኖ ላይ በስተግራ ጥግ ከፍ ብለው የሚታዩትን ሶስት ብርትኳናማ መስመሮች ይጫኑ!


የግላዊነት ፖሊሲ

ሶስተኛው የሲንባድ ጉዞ


ቀዳሚ ክፍል፡ ሁለተኛው የሂንባድ ጉዞ


አሁንም ብዙ ሳልቆይ ስንፍና እና ድግግሞሽ በተሞላበት ህይወት መቀጠል ስለሰለቸኝ እራሴን አበረታትቼ እና የባህር ፍርሃቴን ተቋቁሜ በድጋሚ ከነጋዴዎች ጋር ሌላ ረዥም የባህር ላይ የንግድ ጉዞ ጀመርኩ።

ብዙ ወደቦች ላይ እያረፍንም አትራፊ የንግድ ስራዎችን ሰራን።

አንድ ቀን ከፍተኛ የሆነ የባህር መናወጥ ተከሰተና ለብዙ ቀናት አናወጠን; የመርከባችንን አቅጣጫም በግድ ቀይሮ ወደ አንድ ደሴት ወሰደን። የመርከባችን ካፕቴን በፍጹም እዚህ ደሴት ላይ ማረፍ ባይፈልግም ምንም አማራጭ ስላልነበረን መልህቃችንን ጥለን ወረድን።

ከመርከባችን እንደወረድንም ካፕቴናችን ያለንበት ደሴት እና ሌሎች አጎራባች ደሴቶች በጸጉራም አውሬዎች የተሞሉ እንደሆኑ እና እኚህ አውሬዎች እኛን ከማጥቃት በፍጹም ወደኋላ እንደማይሉ ነገረን። 

"ከመጡም በፍጹም ልታጠቋቸው እንዳትሞክሩ; ብዛታቸው እንደአንበጣ መንጋ ስለሆነ አንችላቸውም, ከነሱ አንዱን ብንገል ተባብረው በአንድ ጊዜ ነው ተባብረው የሚያጠፉን" አለን!

ይሄን ተናግሮ እንደጨረሰም መላ ሰውነታቸው በቀይ ጸጉር የተሸፈነ; በቁጥርም እጅግ የበዙ አውሬዎች እየዋኙ መጥተው መርከባችንን ወረሩ; በዚህም ካፕቴናችን ያለን ነገር ሁሉ እውነት መሆኑን አወቅን።

ምን እንደሆነ በማናውቀው ቋንቋ እየተንጫጩ ከበቡን; በሚያስገርም ፍጥነትም የመርከባችንን ጎን ተንጠላጥለው ወጡ።

ሸራችንን አውርደው, ገመዱን ቆርጠው በጉተታ ከባህሩ ዳርቻ ወስደው ከመርከቡ እንድንወርድ አደረጉን። 

ቀደሴቱ ላይ እየተጓዝንም ከርቀት ግዙፍ ህንጻ ይታየን ነበር። ያን ግዙፍ ህንጻ ስንቀርበውም በጥሩ ጥበብ የተሰራ ትልቅ ቤተ-መንግስት ሆኖ አገኘነው! 

በሩም ግዙፍ እና ከሁለት ጥቁር እንጨቶች የተሰራ!

ከፍተነው እንደገባንም ወደ አንድ ሰፊ አዳራሽ መጣን; ከፊትለፊታችንም ስጋ መጥበሻ ቦታ, ብዙ ጦሮች እና ክምር የሰው አጽም አየን!

በአየነውም ነገር እጅግ ተሸበርን! 

ይዘውን የመጡት ጸጉራም አውሬዎችም በሩን ዘግተውብን ሄዱ።

ብዙም ሳይቆይ ግን በሩ ድጋሚ በታላቅ ሀይል ብርግድ ተደርጎ ተከፈተ; ከዘምባባ ዛፍ የሚበልጥ ረዥም እና ግዙፍ ፍጡር ገባ።

ይህ ፍጡር ከግንባሩ መሀል የተቀመጠ አንድ አይን ብቻ ሲሆን ያለው እሱም እንደፍም በጣም የቀላ ነበር! ጥርሶቹም ረዣዥም እና ሹል ናቸው, ከአፉም ውጪ ሆነው ይታዩ ነበር። የታችኛው ከንፈሩ ተንጠልጥሎ ወርዶ ከደረቱ የደረሰ ነበር! ጆሮወዎቹም እንደዝሆን አይነት ሆነው ትከሻዎቹን ሸፍነዋቸዋል!  ጥፍሮቹም እንደግዙፍ ወፍ ስለታማ: የታጠፉ እና እጅግ ሲበዛ አስፈሪ ነበሩ!

በተመለከትነው ነገር ደንግጠን እንደበድን ደርቀን ቀረን!

ከበድንነታችን መለስ ስንል ጥግ ተቀምጦ አፍጥጦ ሲያየን አገኘነው።

ብድግ ብሎ ወደኛ መጣና መጀመርያ እኔን ማጅራቴን ይዞ አነሳኝ; በግ የሚገዛ ይመስል አገላብጦ ከተመለከተኝ በኋላ ቀጫጫ እና የተሰራሁትም ከቆዳ እና አጥንት ብቻ መሆኑን ሲያይ መልሶ ለቀቀኝ።

በመቀጠል ሌሎቹንም በተራ በተራ እያገላበጠ ከተመለከተ በኋላ ካፕቴናችን ላይ ደረሰ።

ካፕቴናችን ከሁላችንም ወፍራም ስለነበረ አገላብጦ ካየው በኋላ ጦር አንስቶ ሰካበት እና አይናችን እያየ ጠብሶ በላው!

በልቶት እንደጨረሰም በሩጋ ሄደና እንደነጎድጓድ እያንኮራፋ አንቀላፋ እስከጠዋት ድረስ ተኛ!

ለእኛ ግን ማረፍ ፈጽሞ የማይታሰብ ነገር ሆነብን, ለሊቱንም በታላቅ ፍርሀት ስንርድ አሳለፍን!

እንደነጋም አውሬው በጠዋት ተነስቶ ወጣና ጥሎን ሄደ።

በሚመጣው ምሽትም ራሳችንን ለማዳን ወስነን የሚከተለውን አደረግን;

ተመልሶ መጥቶ አንዳችንን በድጋሚ መርጦ ከበላ በኋላ በጀርባው ተንጋሎ አንቀላፋ! ልክ ማንኮራፋት እንደጀመረ ከመሀከላችን ፈርጠም ፈርጠም ያልነው ተመራርጠን በጣም ሹል የሆኑ ጦሮች መርጠን አንዳንድ ያዝን እና እሳቱ ውስጥ ከተን ፍም እስኪመስሉ አጋልናቸው።  በመቀጠልም እኩል ተንደርድረን ሄደን ግንባሩ መሀል ያለችው አንድ አይኑ ውስጥ ከተትናቸው።

ህመሙ በታላቅ እና ነጎድጓዳማ ጩኸት እንዲነሳ አደረገው! እየተወራጨ እና አየዳሰሰም ሊይዘን ፈለገን; እኛ ግን ሊደርስ በማይችልባቸው ቦታዎች ተደብቀን ስለነበር ሊያገኘን አልቻለም።

በመጨረሻም በሩን ከፍቶ በታላቅ ህመም እየጮኸ ሄደ!

ወዲያውኑ እንደወጣ ቤተመንግሥቱን ለቀን በመሮጥ ወደ ባህሩ ዳርቻ መጣን: እንደደረስንም የጣውላ ክምር ስላገኘን ሶስት ሶስት ሰው መያዝ የሚችሉ ታንኳዎች ሰራን። የሰራናቸው ታንኳዎች ላይም ወጥተን ጉዞ ከመጀመራችን በፊትም አውሬው ከሞተ በሚል ተስፋ እስኪነጋ ድረስ እዛው ለመጠበቅ ወሰንን።

የአውሬው ጩኸት ይሰማን ስለነበር ጠዋት ካልመጣ ወይንም መጮሁን ካቆመ ሞቷል ማለት ነው; እንደዛ ከሆነ ደግሞ ከመሄድ እና ህይወታችንን አደጋ ላይ ከመጣል እዚሁ ደሴት ላይ መቆየት ይሻለናል ብለን አስበን ነበር።

ሆኖም ግን ገና ሳይነጋጋ ጠላታችንን ከሩቅ አየነው; ብቻውን  አልነበረም ይብስ ብሎ ሌሎች በጣም ብዙ እሱን መሰል አውሬዎች ጋር በፍጥነት ወደኛ እየመጡ ነበር።

ባለን ፍጥነት ሁሉ ታንኳዎቻችንን ወደ ባህሩ ጎትተን ገብተን መጓዝ ጀመርን! ይህንን የተመለከቱት አውሬዎችም ትላልቅ ቋጥኞችን እያነሱ ወረወሩብን: ስንርቃቸውም እስከወገባቸው ድረስ ባህሩ ውስጥ ገብተው ቋጥኝ ወረወሩብን።

ሲወረውሩብንም በጣም ኢላማቸውን ጠብቀው ስለነበር እኔና ሁለት ጓደኞቼ ካለንበት አንድ ታንኳ በስተቀር ሌሎቹ ሁሉ ተመተው ሰመጡ።  እኛም በተቻለን አቅምና ፍጥነት ቀዝፈን ከአደጋው ተረፍን።

ከግዙፎቹ አውሬዎች ብናመልጥም ሰፊው ባህር ላይ በንፋስ እና ወጀብ እየተንገላታን; ወዴት እንኳን እንደምንሄድ ሳናውቅ እጣ ፈንታችንን በመጠባበቅ ቀኑን እና የሚከተለውን ምሽት አሳለፍን።

በሚቀጥለው ጠዋት ግን እንደመታደል ሆኖ ወደ አንድ ደሴት በማእበል ተገፍተን አረፍን። በዚህም እጅግ ደስተኞች ሆንን! 

እዚህ ደሴት ላይ የሚጣፍጡ ፍራፍሬዎችን አግኝተን ተመገብን!

ሲመሽ የባህሩ ዳርቻ ላይ አንቀላፋን። ለሊት ግን በጣም ትልቅ ርዝመት እና ዘግናኝ ድምጽ ባለው እባብ ከእንቅልፋችን ተቀሰቀስን። እባቡ በመሬት ሲሳብ ሰውነቱ ላይ ያለው ቅርፊት የመፋተግ ድምጽ ያሰማ ነበር!

ከጓደኞቼ አንዱን ለማምለጥ ቢታገልና ቢጮህም ከመሬት ጋር ደጋግሞ እያላተመ እና እያጋጨ ዋጠው።

ከቦታው ሸሽተን ብዙ ብንርቅም የጓደኛችን ስቃይ ይሰማን ነበር።

በማግስቱም እባቡን አየነው!

"አምላኬ ሆይ ምን ላይ ነው የጣልከን? ከግዙፍ አውሬ እና ከባህር ማእበል ተረፍን ብለን ተደስተን ሳንጨርስ እንዲህ ያለ ሌላ ችግር ውስጥ ትከተናለህ?" ብዬ አማረርኩ!

ደሴቱ ላይ ስንዘዋወር አንድ ግዙፍ ዛፍ አገኘን; ለደህንነታችንም ስንል ቀጣዩን ምሽት እዛ ዛፍ ላይ ወጥተን ለማሳለፍ ወሰንን። ዛፉ ላይ ወጥተን ተኝተንም ሳለ እባቡ "ሂስስስስስ..." እያለ ከዛፋ እግር ስር መጣ!

ከኔ ዝቅ ብሎ ተኝቶ የነበረውን ጓደኛዬንም ዋጥ አደረገውና ሄደ!

እስኪነጋ ድረስ ዛፉ ላይ በፍርሀት እንደሬሳ በድን ሆኜ ቆየሁና ሲነጋ እንደዛው ሆኜ ወረድኩ!

ከዛም ጓደኞቼ ላይ የሆነውን ሳስብ እጅግ ስለፈራሁ እና ስለተጨነኩ ወደባህሩ ሄጄ ራሴን ላጠፋ አሰብኩ። ሆኖም ግን ህይወት ፈጣሪም ወሳጅም አምላክ ስለሆነ እስካለሁ ድረስ ልታገል ወስኜ ተውኩት።

በመቀጠልም እጅግ በጣም ብዙ እሾሀማ ቁጥቋጦ እና ቅርንጫፍ ለቃቅሜ በዛፉ ዙሪያ ሰፊ ክብ ሰራሁ! ተጨማሪ እሾሀማ ቅርንጫፎችንም የምተኛበት የዛፉ ቅርንጫፍ ዙሪያ አንጠለጠልኩ።

ይህንንም አድርጌ ከጨረስኩ በኋላ ሲመሽ ዛፉ ላይ ወጣሁና ተኛሁ! 

እባቡ በተለመደው ሰአት መጣ; ዛፉንም እየተሽከረከረ ሊበላኝ ፈልጎ መግቢያ ማፈላለግ ጀመረ። ሆኖም ግን የሰራሁት አጥር አላሳልፍ ስላለው አይጥ ቀዳዳ ውስጥ ገብታ እንዳመለጣች ድመት ሲያየኝ ቆይቶ ሊነጋጋ ሲል ሄደ።

እኔ ግን ጸሀይ ሙሉ ለሙሉ እስክትወጣ ድረስ ከዛፉ ለመውረድ አልደፈርኩም ነበር!

ተስፋ መቁረጤ በዝቶ እራሴን ወደባህሩ ልወረውር ስል አምላክ ምህረት አደረገልኝ! ከርቀት አንድ መርከብ አየሁ!

ላንቃዬ እስኪሰነጠቅ ጮሄ እና እንዲያዩኝ ጥምጣሜን ፈትቼ እያውለበለብኩ መጣራት ጀመርኩ።

ተሳክቶልኝም አዩኝና የመርከቡ ካፕቴን ጀልባ ልኮልኝ ወደ መርከቡ ተወሰድኩ። መርከቡ ላይ እንደወጣሁም ነጋዴዎች እና ባህርተኞች እንዴት ወደዚህ ሩቅ ደሴት እንደመጣሁ ለማወቅ ያለሁበት መጥተው ተሰበሰቡ። የገጠመኝን ከነገርኳቸው በኋላም ከተጓዦቹ ጠና ያለው ሽማግሌ ስለግዙፎቹ አውሬዎች ሲወራ እንደሰማ እና ሰው በላ አውሬዎች መሆናቸውን ነገረን። እባቦቹ ደግሞ እኔን ባገኙኝ ደሴት ላይ እጅግ በጣም ብዙ እንዳሉና ቀን ቀን ተደብቀው ሲመሽ እንደሚወጡ ነገረን።

በመትረፌ እንደተደሰቱ ከነገሩኝ እና ጥሩ ምግብ እና መጠጥ ከሰጡኝ በኋላ ወደካፕቴናቸው ወሰዱኝ። እሱም የለበስኩት ቡትቶ መሆኑን ካየ በኋላ ከራሱ ልብስ አንዱን ሰጠኝ እና ለበስኩ። 

ከተረጋጋሁ በኋላም በደንብ አድርጌ ካፕቴኑን ሳየው: በሁለተኛ ጉዞዬ ላይ ከዛች ደሴት ለማረፍ በተኛሁበት ጥሎኝ የሄደው ካፕቴን ሆኖ አገኘሁት።

ሞቷል ብሎ ስላመነም አይቶ ስላላወቀኝ አልገረመኝም!

"ካፕቴን?" አልኩት...
"እስኪ በደንብ እየኝ! ባለፈው እዛች ደሴት ላይ ጥለኸኝ የሄድከው ሲንባድ ነኝኮ!" አልኩት።

ካፕቴኑ በደንብ አጢኖ ካየኝ በኋላም አወቀኝ!

"እግዚአብሔር ይመስገን" ብሎ ጮኸና አቀፈኝ! 

"እድል ጥፋቴን ስላቃናችልኝ እግዚአብሔር ይመስገን!" ብሎ ድጋሚ ጮኸ

በመቀጠልም "ይኸው ንብረትህ በእንክብካቤ አንዳች ሳልነካ አስቀምጬልሀለሁ" ብሎ ያኔ የነበረኝን ንብረቴን መለሰልኝ።

ተቀብዬውም ስለተንከባከበልኝ ከልቤ አመሰገንኩት!

በባህር ላይ ለትንሽ ጊዜ ተንቀሳቅሰን ብዙ ደሴቶችን ጎበኘን; ተገበያየንባቸውም። ከጎበኘናቸው ደሴቶች አንዷ ብዙ የመድሀኒት ዛፎይ እና ቅጠሎች የሚገኙባት የሳላባት ደሴት ነበረች።

ከዛ ቀጥሎም ቅሩንፉድ: ቀረፋ እና ሌሎች ቅመማ ቅመሞችን ከሌላ ደሴት ገዛሁ። በጉዟችንም ሁያ ሜትር ስፋት እና ርዝመት ያለው ኤሊ ተመለከትኩ። ላም የሚመስል ውሃ ውስጥ እና መሬት ላይ የሚኖር ወተት የሚሰጥ ቆዳውም ጠንካራ ከመሆኑ የተነሳ ታንኳ የሚሰራበት እንሰሳ አየሁ። ሌላም የግመል መልክ እና ቀለም ያለው እንሰሳ አይቻለሁ።

በአጭሩ ረዥም ጉዞ ተጉዤ ቡሶራ ገባሁ! ከዛም ከምንጊዜውም በላይ ብዙ ሀብት አካብቼ ወደምወዳት ባግዳድ ተመለስኩ።

ስደርስም ለድሆች ብዙ ለግሼ ለራሴም ሰፊ ሀብት አካበትኩ!

በዚህም ሲንባድ የሶስተኛ ጉዞውን ትረካ ጨረሰ። ሌላ መቶ አልማዞች ለሂንባድ ሰጥቶም በማግስቱ ለእራት መጥቶ የአራተኛውን ጉዞውን ታሪክ እንዲሰማ ጋበዘው።


ቀጣይ ክፍል: አራተኛው የሲንባድ ጉዞ



ተጨማሪ አዳዲስ ታሪኮች

አእምሮና ምናገባህ: Amharic tales for Children

ምናገባህ እና አእምሮ

ጥጃው ሳምሶን: Amahric story for children

ጥጃው ሳምሶን

የስሜት ህዋሳት ጸብ: Amharic tale

የስሜት ህዋሳት ጸብ

Ethiopian National Flag

የኢትዮጵያ ህዝቦች ብሄራዊ መዝሙር

Teaching about maps

ካርታ ምንድነው?

Water cycle (የውሃ ኡደት)

የውሃ ኡደት (Water cycle)

ዉቢት እና ጭራቁ: Amharic tales for children

ውቢት እና ጭራቁ

ሰባተኛው እና የመጨረሻው የሲንባድ ጉዞ: Amharic tales

ሰባተኛው እና የመጨረሻው የሲንባድ ጉዞ

search

ተረት መፈለግያ