leljoch.com Logo

LELJOCH.COM

ጤና ይስጥልን! ድህረ ገጻችንን ለመጠቀም በመለያ መግባት አለቦት፡፡

በመለያ ለመግባት ወይንም አዲስ መለያ ለመፍጠር እስክሪኖ ላይ በስተግራ ጥግ ከፍ ብለው የሚታዩትን ሶስት ብርትኳናማ መስመሮች ይጫኑ!


የግላዊነት ፖሊሲ

ውቢት እና ጭራቁ

በድሮ ዘመን ስድስት ልጆች የነበሩት አንድ ሀብታም ነጋዴ ነበር። ሶስት ልጆቹ ወንዶች ሲሆኑ ሶስቱ ደግሞ ሴቶች ነበሩ።

ይህ ሀብታም ሰው ብልህ ስለነበር ልጆቹ ሁሉ በዘመኑ ጥሩ የተባለ ትምህር ከብዙ መምህራን እንዲያገኙ አድርጎ ነው ያሳደጋቸው። ከስድስቱ ልጆቹ የመጨረሻዋ ልጅ እጅግ በጣም ውብ ነበረች; ከልጅነቷም ጀምሮ ሰዎች በውበቷ ይደነቁና "ትንሿ ውቢት" እያሉ ይጠሯት ነበር። ስታድግም ሰው ሁሉ ውቢት እያለ ይጠራት ጀመር; በዚህ ምክንያት ሁለት እህቶቿ አብዝተው ይቀኑባት ጀመር። 

ዉቢት ከውበቷ በተጨማሪ ለእህቶቿ እጅጉን መልካም ነበረች። ሁለቱ እህቶቿ ግን ሰነፎች በሀብታቸው የሚመኩ እና ሰውን የሚንቁ ነበሩ።

በዚህም የተነሳ ከሌሎች ነጋዴዎች ልጆች ጋር አይቀራረቡም ነበር; ጓደኛ የሚያደርጉትም በጣም ብዙ ሀብት ያላቸውን ሰዎች ብቻ ነበር። በየቀኑ ለመዝናናት ወደ ውድ ውድ ቦታዎች  እና ትልልቅ ድግሶች ይሄዱ ነበር። ውቢት ብዙ ጊዜዋን በንባብ ስለምታሳልፍም ይሳለቁባት ነበር። ከአባታቸው የሚወርሱት ሀብት ታላቅ ስለነበር በጣም ብዙ ሀብታም ነጋዴዎች የጋብቻ ጥያቄ አቅርበውላቸው ነበር እነሱ ግን ንጉስ ካልሆነ እሱ ቢቀር እንኳ ልኡል ካልሆነ በጭራሽ አናገባም አሉ።

ውቢት እናግባሽ ብለው የመጡትን በትህትና አናግራ እና ገና ለጋብቻ ያልደረሰች ልጅ መሆኗን አብራርታ በተጨማሪም ተጨማሪ አመታትን ከአባቷ ጋር መቆየት እንደምትፈልግ እየተናገረች ትመልሳቸው ነበር።

በድንገት ነጋዴው ከሰረና ከከተማ ራቅ ባለ ገጠር ከምትገኝ አንዲት ጎጆው በስተቀር ሁሉንም ሀብት ንብረቱን አጣ። አይኖቹ እንባባ አቅርረውም ሁኔታውን ለልጆቹ አስረዳና እራሳቸውን ለማኖር ወደ ገጠር ሄደው መስራት እንዳለባቸው ነገራቸው።

ሁለቱ እህትማማቾች ከተማ ያሉ ወዳጆቻቸውን ተማምነው ገጠር ሄደው መኖር እንደማይፈልጉ ተናገሩ። ነገር ግን በኩራታቸው ምክንያት ሰው አይወዳቸውም ነበር እና የከተማ ወዳጆቻቸው በችግራቸው ጊዜ ራቋቸው።

ለሁለቱ እህትማማቾች ያዘነ ሰው አልነበረም; እንደውም ኩራታቸው ተንፍሶላቸው ዝቅ ብለው ስለታዩ ሰው ሁሉ ተደሰተ። ሲኖራቸው እንዲህ ጨምላቃ ከሆኑማ ገጠር ሄደው ከብት እያለቡ እና በእበት እየወለወሉ ይኑሩ ሲሉ ፈረዱባቸው። 

ለውቢት ግን ከልብ አዘኑላት። መልካምነቷን ሰው አቅራቢነቷን እና ለድሆች አዛኝነቷን እያወሱም መልካሙን ሁሉ ተመኙላት።

በጣም ብዙ ሰዎች ምንም እንደሌላት ቢያውቁም ለውቢት የጋብቻ ጥያቄ አቀረቡላት። ነገር ግን ውቢት አባቷን በችግሩ ጊዜ ልትተወው እንደማትችል እና ገጠር አብራው ሄዳ ልትንከባከበው መወሰኗን በማሳወቅ የቀረቡላትን ጥያቄዎች ሁሉ ውድቅ አደረገች። 

በመጀመርያ ውቢት ሀብት እና ንብረቷን ድንገት ስላጣች በጣም አዝና ነበር። ነገር ግን ማልቀስ ምንም ለውጥ እንደማይፈጥር ስላወቀች ሀብት ባይኖራትም እራሷን ደስተኛ አድርጋ ለመኖር ወሰነች።

ገጠር እንደደረሱ ነጋዴው እና ሶስቱ ወንዶች ልጆቹ ገበሬዎች ሆኑ። ውቢትም በየቀኑ ከሌሊቱ 11 ሰአት እየተነሳች ለቤተሰቡ ቁርስ ማዘጋጀት እና ቤቱን ከማጸዳዳት ጀምሮ ሌሎች የተለያዩ ስራዎችን በመስራት ማገዝ ጀመረች። እንደዚህ ያለ ኑሮ ስላለመደች መጀመርያ ላይ በጣም ከብዷት ነበር። በሁለት ወራት ውስጥ ግን ሁሉን ነገር ለምዳው ከምን ጊዜውም በተሻለ ሁኔታ ጠንካራ እና ጤናማ ሆነች።

ስራዋን ስትጨርስ ታነብ, ፒያኖ ትጫወት እና ዥዋዥዌ እየተጫወተች ትዘፍን ነበር።

በተቃራኒው ደግሞ ሁለት እህቶቿ የሚሰሩት ጠፋባቸው። አርፍደው ከንጋቱ 4 ሰአት ከእንቅልፋቸው ነቅተው ቀኑን በመዞር እና ያጧቸውን ውድ ውድ ልብሶች, ሀብት, ወዳጅ ዘመዶች እና የተንደላቀቀ ኑሮ እያወሱ ሲያላዝኑ ይውላሉ። ውቢትንም በገጠማቸው አሳዛኝ ሁኔታ ውስጥ ሰላም አጊኝታ ስለኖረች ይሰድቧት እና ያንቋሽሿት ነበር።

ነገር ግን ነጋዴው አባታቸው ስለ ውቢት ከሁለቱ እህትማማቾች የተለየ አስተያየት ነበረው። በመልክም ሆነ በባህሪ ከሁለቱ እህቶቿ የተበለጠች እንደሆነች ያውቅ ነበር። ትህትናዋን, ጠንካራ ሰራተኝነቷን እና ታጋሽነቷንም ያደንቅላት ነበር።

እህቶቿ የቤቱን ስራ ሙሉ ለሙሉ ለዉቢት መተዋቸው ሳያንስ ይሰድቧት እና ያንቋሽሿትም ነበር።

ለአንድ አመት ያክል እንደዚህ ከኖሩ በኋላ ንብረቶቹን የጫነ በርከብ ዘደብ መድረሱን የሚገልጽ ደብዳቤ ለአባታቸው ደረሰው። ይህ ዜና ሁለቱን እህትማማቾች እጅግ በጣም አስደሰታቸው። ወዲያውም ወደ ከተማ ተመልሰው ስለመኖር ማለም ጀመሩ። የገጠር ህይወት በጣም ሰልችቷቸው ነበር። አባታቸውን አዳዲስ ልብሶች, ቆቦች, ጌጣጌጥ እና ሌሎች የምቾት ነገሮችንም እንዲገዛላቸው በተራ በተራ አከታትለው ጠየቁት።

ውቢት ግን አባቷ የሚወስደው ገንዘብ እንደማይበቃው ስላወቀች ምንም አልጠየቀችውም ነበር።

"ላንቺስ ምን ላምጣልሽ ውቢት?" አላት አባቷ...

"ካሰብከኝ አይቀር ጽጌሬዳ አበባ አምጣልኝ። እዚህ አካባቢ ስለማይበቅል እሱ ይበቃኛል።" አለችው. . .

ውቢት አበባውንም የጠየቀችው ፈልጋ ሳይሆን ምንም አልፈልግም ካለች እህቶቿን እየወቀሰች እንዳይመስልባት ፈርታ ነው።

ነጋዴው አባታቸው ተጉዞ ሄደና ንብረቱ ካለበት ሲደርስ በንብረቱ ዙሪያ ሌላ የህግ ጭቅጭቅ ውስጥ ገባና ተሸንፎ ሲሄድ ድሃ እንደነበር ሲመለስም እንደዛው ድሃ ሆኖ ወደ ቤቱ ተመለሰ።

ነጋዴው ወደ ቤቱ ሊደርስ ወደ ሀምሳ ኪሌሜትሮች ያህል ሲቀሩት ልጆቹን ለማግኘ ጓጉቶ በመጓዝ ላይ ሳለ ጫካ ውስጥ ጠፍቶ ያለበትን ማወቅ ተሳነው። አየሩም ድንገት ተቀያየረና በረዶ እና ዝናብ ቀላቅሎ መጣል ጀመረ። ከባድ ነፋስም መጣና ደጋግሞ ከፈረሱ ላይ ጣለው። እየመሸ በመጣ ቁጥር በቅዝቃዜ ወይንም በርሃብ እንዳልሞት ብሎ ፈራ። ከሱ ይልቅ ግን እየከበበው የመጣው የተኩላ ጩኸት አስጨነቀው።

በድንገት ከርቀት በዛፎቹ መሀል የብርሃን ጭላንጭል ተመለከተ። ወደ ብርሃኑ ትንሽ እንደተጓዘም ብርሃኑ የሚመነጨው ከላይ እስከ ታች በመብራት ካሸበረቀ ግዙፍ እና የሚያምር ቤት መሆኑን ተመለከተ።

ነጋዴው አምላኩን እያመሰገነ በፍጥነት ወደተመለከተው ቤት ፈረሱን ይዞ ተጓዘ። ግቢው ውስጥ ማንንም አለማግኘቱ እጅጉን አስደነቀው። ፈረሱ ትልቅ እና ክፍት የመኖ ቤት ስላየ በጣም ተርቦ ነበር እና ወደዛ ገብቶ ድርቆሽ እና አጃ መመገብ ጀመረ።

ነጋዴው ወደ ቤቱ ውስጥ ዘልቆ ገባ።

በቤቱ ውስጥ የቀጣጠለ እሳት የሚንቦገቦግበት ጥሩ ሰውነት ማሞቂያ ስፍራ እና ጠረጴዛ ላይ ለአንድ ሰው ተዘጋጅቶ የተቀመጠ ምግብ  በሰፊ ሳሎን ውስጥ አገኘ። 

በዝናብ እና በረዶው በስብሶ ስለነበር የቤቱ ባለቤት ወይንም አገልጋይ ከመጡ ሁኔታዬን ይረዱኛል በሚል ተስፋ ወደሚቀጣጠለው እሳት ሄዶ መሞቅ ጀመረ።

ነጋዴው ለረጅም ጊዜ ቢጠብቅም ማንም አልመጣም። ከምሽቱ አምስት ሰአት እስኪሆን ቢጠብቅም ብቅ የሚል ሰው ስላልነበር እና ርሃቡንም መቋቋም ስላልቻለ ጠረጴዛው ላይ ተቀምጦ የነበረውን ምግብ በሁለት ጉርሻ ጨረሰው። ይህንን ሲያደርግ በታላቅ መጨነቅ እና ፍርሃት ውስጥ ሆኖ ነበር።

ምግቡን ከበላ በኋላ ጥቂት ብርጭቆ ወይን ጠጣና ብርታቱ ተመለሰለት። አሁን ትንሽ ድፍረት ስላገኘም የነበረበትን ሳሎን ትቶ ብዙ በሚያማምሩ የቤት እቃዎች እና ጌጦች የተሞሉ ትላልቅ እና የተዋቡ ክፍሎችን አልፎ ተጓዘ። በስተመጨረሻም በጣም ምቹ እና ግዙፍ አልጋ ወዳለበት ክፍል ገባ።

በጣም ደክሞት ስለነበር እና እኩለሌሊትም አልፎ ስለነበር የክፍሉን በር ዘግቶ ለመተኛት የዛለ ሰውነቱንም ለማሳረፍ ወሰነ።

በበነጋው ጠዋት ሁለት ሰአት ሊሆን ሲቃረብ ነጋዴው ከእንቅልፉ ሲነቃ ክፍሉ ውስጥ ንጹህ እና በስነስርዓት ተጣጥፈው የተቀመጡ ልብሶች ማግኘቱ ደነቀው። የተበላሸ ልብሱን የሚቀይርበት ስላገኘም
"እርግጠኛ ነኝ ይህ ቤት የችግር ደራሽ መላእክ ቤት ነው። ችግር እና መከራዬንም አይቶ ሊረዳኝ ወስኖ መሆን አለበት።" አለ 

በመስኮት ሲመለከትም በበረዶ እና ጭቃ ፈንታ በጣም ሰፊ እና በአበቦች ያሽቆጠቆጠ ግቢ ተመልክቶ እጅጉን ተደነቀ። እራቱን ወደተመገበበት አዳራሽ ሲመለስ ጥሩ ቁርስ ቀርቦ ጠበቀው። 

"መልአክ ወይ ስላሰብክልኝ እና ቁርስ ስላቀረብክልኝ, ስለመልካምነትህ ሁሉ ከልብ አመሰግናለሁ!" አለ።

ነጋዴው ቁርሱን በልቶ ፈረሱን ፍለጋ ሄደ። በአበቦች በተሞላው ግቢ ሲያልፍም ውቢት ያለችው ትዝ አለውና ብዙ የጽጌረዳ አበቦች የያዘ አንድ ቅርንጫፍ መርጦ ቆረጠ። ወዲያውኑም ታላቅ ጩኸት ተሰማ እና አስደነገጠው;  አንድ ጭራቅም ወደሱ ሲመጣ ተመልክቶ ራሱን ስቶ ለመውደቅ ጫፍ ደረሰ።

"እጅግ ሲበዛ ምስጋና ቢስ ነህ!" ብሎ በሚያስፈራ ድምጽ ጮኸበት ጭራቁ...

"ህይወትህን አድኜ ወደቤቴ ባስገባህ ከምንም ነገር አስበልጬ የምወዳቸውን የጽጌረዳ አበቦች ተቀጥፍብኛለህ? ለዚህ ጥፋትህ ቅጣትህ ሞት ነው። በል 15 ደቂቃ ሰጥቼሀለሁ ጸሎተትህን ለአምላክህ አድርስ።" 

ነጋዴው በጉልበቱ ተንበርክኮ እና ሁለት እጆቹን ወደ ላይ አንስቶ እያለቀሰ
"እባክህ ጌታዬ ይቅር በለኝ። ላበሳጭህ ወይ ልጎዳህ ፈልጌ አልነበረም አበባ የቀጠፍኩት ከሴት ልጆቼ አንዷ የጽጌረዳ አበባ አምጣልኝ ስላለችኝ ለሷልወስድላት ፈልጌ እንጂ።" አለና ለመነው

"ስሜ ጭራቁ እንጂ ጌታዬ አይደለም። በማንቆለጳጰስ የሚደረግ ልመና አልወድም! እውነት የሚናገር ሰው ግን ይመቸኛል። ስለዚህ ልመናህ ውሳኔዬን የሚያስቀይረኝ እንዳይመስልህ። በልጆችህ ስለለመንከኝ በአንድ ቅድመ ሁኔታ ልምርህ ፍቃደኛ ነኝ። እሱም ከነሱ አንዷ በፍቃዷ ትምጣና በአንተ ቦታ ራሷን ትሰዋልህ። ልመናህን ትተህ ከልጆህ አንዷ ባንተ ቦታ ለመሰዋት ፍቃደኛ ካልሆነች በሶስት ወር ውስት ራስህ ተመልሰህ ልትመጣ ቃል ግባልኝ።"

ነጋዴው ሴት ልጆቹን ፈጽሞ ለጭራቁ የሚሰጥ ባይሆንም ልጆቹን ለመጨረሻ ጊዜም ቢሆን የሚያይበት አጋጣሚ ስላገኘ ለጭራቁ እንደሚመለስ ማለለት። ጭራቁም ባሰኘው ጊዜ መሄድ እንደሚችል ነግሮት...

"ነገር ግን ባዶ እጅህን ከምትመለስ ወዳደርክበት ክፍል ተመለስና ትልቅ ባዶ ሳጥን ታገኛለህ። ይጠቅመኛል ባልከው ነገር ሁሉ ሙላው እኔ ወደ ቤትህ እልክልሀለሁ።" አለውና ሄደ።

ነጋዴውም ለራሱ

"መሞቴ ካልቀረማ ለልጆቼ የሆነ ነገር ልተውላቸው።" ብሎ አሰበ!

በመቀጠልም ምሽቱን ወዳሳለፈበት ክፍል ሄዶ እንደተባለው ትልቅ ባዶ ሳጥን አገኘ። ከዛም በጣም ብዙ የወርቅ ሳንቲሞች አገኘና ጭራቁ እንደነገረው ሳጥኑን ሞልቶት በደንብ ቆለፈውና ፈረሱን ይዞ በጥልቅ ሀዘን እንደተሞላ ከግዙፉ እና የተንደላቀቀው ቤት ወጥቶ ሄደ።

ፈረሱ በራሱ የሚሄድ በሚመስል ሁኔታ ከጫካው ወጣና በጥቂት ሰአታት ውስጥ ነጋዴውን ሰውዬ ቤቱ አደረሰው። 

ልጆቹ አባታቸውን ሲያዩት በደስታ ቢከቡትም እሱ ግን በሀዘን ተውጦና በእጁ ጽጌሬዳ አበባ ይዞ ተመለከታቸው። አይኖቹ በእንባ ተሞልተውም 

"ውቢት እንኪ ይኸው ጽጌሬዳ አበባሽ። አባትሽ ምን ያህል ዋጋ እንደከፈለበት ባወቅሽ!" አለ ለውቢት የያዘውን አበባ እየሰጣት።

ቀጥሎም የገጠመውን ሁሉ ለልጆቹ ነገራቸው!

ታሪኩን እንደሰሙ ሁለቱ እህትማማቾች በጣም አለቀሱ ውቢትንም ያንቺ ጥፋት ነው ብለው ብዙ ክፉ ነገር ተናገሯት። ውቢት ግን ይህ ሁሉ ሲሆን ፍጹም መረጋጋት ውስጥ ሆና አንዲት እንኳን እንባ አለውጣትም ነበር።

"እዩልን የዚህችን እርጉም ልጅ ነገር። እንደኛ ልብስ እና ጌጥ በመጠየቅ ፈንታ ስትቀብጥ አባታችንን የማይሆን ነገር አዛው ልታስገድልብን ነው። ይህን ሁሉ አጥፍታም ግን አታለቅስም!" አሉ።

"ለምን አለቅሳለሁ?" አለች ውቢት!

"ምን ጥቅም አለው? ባይሆን አባቴ በኔ ፋንታ እንዲሞት አልፈቅድም። ጭራቁ ከሴት ልጆቹ አንዱን ስለጠየቀ እኔ እራሴ ሄዳለሁ። የኔ መስእዋትነት የአባቴን ሀይወት ማትረፉ እና ለሱ ያለኝን ጥልቅ ፍቅር ማሳየቱ ይበቃኛል።" ብላ መለሰችላቸው።

"አይሆንም" ብለው ሶስቱ ወንድሞቿ ተቃወሙ...

"...እንደዛ አይሆንም! እኛ ጭራቁን ፈልገን እንገለዋለን ካልሆነም ልንገለው ሞክረን እንሞታለን።" አሉ።

"እንዲህ ያለ ነገር ለማድረግ ፈጽሞ እንዳታስቡ" አለ ነጋዴው!

"ጭራቁ እጅጉን ግዙፍ እና ሀይለኛ ስለሆነ እሱን ታሸንፉታላችሁ የሚል እምነት የለኝም። የውቢትንም ሀሳብ ምንም እንኳ ፍቅሯን ስላሳየኝ ደስ ቢለኝም ፈጽሞ አልቀበለውም። እኔ አርጅቻለሁ ረጅም እድሜም አይቀረኝም። የሚቆጨኝ ከናንተ መለየቴ ብቻ ነው" አላቸው ነጋዴው አባታቸው

"እኔን ጥለኸኝ በፍጹም ወደ ጭራቁ ቤት አትሄድም በፍጹም ልታስቆመኝ አትችልም" ብላ ውቢት ድርቅ አለች!

ብዙ ተቃውሞ ቢመጣባትም ውቢት ግን ወደ ጭራቁ ቤት ለመሄድ ቆርጣ ስለነበር ልትሰማቸው አልፈቀደችም። 

በውቢት የሚቀኑባት እህቶቿም በሁኔታው ያዘኑ ቢመስሉም ውስጥ ውስጡን ግን በጣም ደስተኞች ነበሩ።

ነጋዴው የሚወዳትን ልጁን የማጣቱ ጉዳይ በጣም አስጨንቆት ስለነበር በወርቅ የተሞላውን ሳጥን ረስቶት ነበር። ሆኖም ግን ማታ ለመተኛት ወደክፍሉ ሲገባ ከአልጋው አጠገብ ተቀምጦ ሲያገኘው በጣም ደነቀው። 

ምንም እንኳን አሁን ተመልሶ የናጠጠ ሀብታም ቢሆንም ወደ ከተማ መመለስ ስላልፈለገ እና ለልጆቹ ከነገራቸው ግን እነሱ ወደ ከተማ መመለስ እንደሚፈልጉ ስለሚያውቅ ጉዳዩን ሚስጥር አደረገው። ይሄንንም ለውቢት ብቻ ነገራት።

ውቢትም ሁለት ወጣቶች እሱ ባልነበረበት ወቅት እየመጡ እህቶቿን እንደሚያገኟቸው ነግራው ጋብቻቸውን እንዲፈቅድ እና ሀብትም እንዲሰጣቸው ለመነችው። ውቢት እህቶቿ ምንም ቢበድሏትም እሷ በጣም ትወዳቸው እና መልካም ስለነበረችም ከልቧ ይቅር ብላቸው ነበር። 

ቅናታሞቹ እህትማማቾች ውቢትን ሲሰናበቷት ያዘኑ ለመምሰል አይናቸውን በሽንኩርት አሽተው የውሸት እንባ እያፈሰሱ ሸኟት። ነገር ግን የውቢት ወንድሞች ከልባቸው ፍጹም አዝነው ነበር።

ውቢት በወንድም እና እህቶቿ ሀዘን ላይ ጭንቀት መጨመር ስላልፈለገች አላለቀሰችም።

ፈረሱ ውቢትን እና አባቷን ይዟቸው ቀጥታ ወደ ጭራቁ ቤት ተጓዘ። ወደ አመሻሽ ሲሆንም እንደከዚህ በፊቱ የጭራቁን ቤት ከርቀት ሲያበራ አዩት። እንደደረሱ ፈረሱ ወደ ማደሪያው በራሱ ሲሄድ እነሱ ወደ ቤቱ ገቡ። ሳሎኑ ውስጥም በሚያምር ሁኔታ የተዘጋጀ እራት የመመገቢያ ጠረጴዛ ላይ ተቀምጦ ጠበቃቸው። 

በስሜት ተሞልቶ ስለነበር ነጋዴው ምግቡ ሊበላለት አልቻለም። ውቢት ግን ከሀዘን ድባብ ለመውጣት ፈልጋ ለአባቷ እና ለራሷ መግቡን አቀራረበች።

እየተመገቡ ሳለም የምግቡን መጣፈጥ እና ብዛት ውቢት ተመልክታ

"ይሄንን ሁሉ ያቀረበልንማ አወፍሮ ሊበላኝ ፈልጎ ነው ማለት ነው።" እያለች አሰበች። በዚህ ጊዜም ከፍተኛ ድምጽ በቤቱ ውስጥ ተሰማና እንደ ገደል ማሚቶ አስተጋባ! አባቷም የጭራቁን መምጣት ሲያውቅ በእንባ ተሞልቶ ልጁን መሰናበት ጀመረ።

ውቢት ጭራቁን ስትመለከት ውስጧ በፍርሀት ራደ። ሆኖም ግን በተቻላት አቅም ራሷን ተቆጣጠረች።

ጭራቁ በፍቃዷ መምጣቷን ጠየቃት። እሳም በፍርሃት በሚንቀጠቀጥ ድምጽ "አ-ዎ-ን" ብላ መለሰችለት።

"መልካም እና ቃልህን አክባሪ ሰው ነህ! ነገ ጠዋት ከዚህ ሂድ ድጋሚ ለመመለስም እንዳታስብ።" አለው ጭራቁ ነጋዴውን ሰውዬ። 

"ቻው ውቢት!" አላት ውቢትን በመቀጠል

"ቻው ጭራቁ!" አለችው እሷም። ወዲያውም ጭራቁ ተሰወረ።

"ወይኔ ውድ ልጄ!" አለ ነጋዴው አባቷ ውቢትን አቅፏት እያለቀሰ!

"ፍርሃቴ ገሎኝ ነበር! እባክሽ አንቺ ሂጂና እኔ ልቅር በቃ እኔን ይግደለኝ!" አላት. . .

ውቢት ግን በቆራጥ ድምጽ "አይሆንም አባቴ! ነገ ጠዋት አንተ ትሄዳለህ እኔን ለአምላክ ጥበቃ ተወኝ።" ብላ መለሰችለት።

ፍርሃት እጅጉን ስለያዛቸው አዳሩን እንቅልፍ እንደማይወስዳቸው እያሰቡ ወደ ማደሪያቸው ቢሄዱም በጣም ከባድ እንቅልፍ ምንም ሳይቆዩ ይዟቸው ሄደ።

ውቢት በህልሟ በጣም የምታምር እና ግርማ ሞገስ ያላት ሴት መጥታ...
"ውቢት, አባትሽን ለማትረፍ የወሰድሽው ከራስ ወዳድነት የጸዳ ውሳኔ አስደስቶኛል። መስእዋትነትሽ ሳይሸለም አያልፍም!" ብላ ተናገረቻት።

ጠዋት ሲነቁ ውቢት ያየችውን ህልም ለአባቷ ነገረችው። ትንሽ ቢያጽናናውም ልጁን ሲሰናበታት ግን አምርሮ ከማልቀስ አላገደውም።

አባቷ ከሄደ በኋላ ውቢት ከግዙፉ ሳሎን ተቀምጣ የእንባ ጎርፍ በጉንጮቿ እየወረዱ ማልቀስ ቀጠለች። ምንም ብታዝንም ቆራጥ ስለነበረች ያንኑ ምሽት ጭራቁ እስኪበላት የቀረቻትን ጊዜ ከጭንቀት ለመራቅ አስባ ጸሎት ጀመረች። 

እራሷንም ለማዘናጋት በግዙፉ ቤት ውስጥ እየተዘዋወረች ግዝፈትና ውበቱን ማድነቅ ጀመረች። እየተዘዋወረች ቤቱን ስትጎበኝም አንድ ግዙፍ በር ተመለከተች, ቀልቧን የሳባትም እላዩ ላይ የተጻፈው "የውቢት ክፍል" የሚል ምልክት ነበር።

በፍጥነት በሩን ከፍታ እንደገባች በክፍሉ ግዝፈት እና ግርማ ሞገስ እጅግ ተደመመች። በክፍሉ ውስጥ ካሉ ነገሮች ሁሉ ቀልቧን የገዟት ግን ግዙፍ ቤተመጽሐፍቱ, ፒያኖው እና ብዙ የሙዚቃ መጽሀፎቹ ነበሩ። 

ለአንድ ቀን ብቻ እንድትቆይ ቢሆን ኖሮ የታሰበው ንህ ሁሉ ዝግጅት እንደማይደረግ አሰበችና ውቢት ብርታት እና መጽናናት ተሰማት። በመቀጠልም ወደ ቤተመጻሕፍቱ ገብታ አንድ መጽሐፍ አንስታ ብታነብ የሚከተለውን አነበበች...

"ውዷ ውቢት እንኳን ደህና መጣሽ
እዚህ  ስለምትወደጅ ፍርሃት አይግባሽ።
ምኞት ፍቃድሽን ብቻ ተናገሪ ሁሌም
አንዳች ሳይፈጸም የሚቀር አይኖርም። "

"ኡፈፈፈፈይ" አለች ውቢት በመገላገል ስሜት...

"አባቴን ድጋሚ ከማየት በላይ የምፈልገው ምንም ነገር የለም።" ብላም ንግግሯን ቀጠለች።

ይህንን ተናግራ እንደጨረሰች ከፊቷ የነበረ ግዙፍ መስታወት ነጸብራቁን ቀየረና የነጋዴው አባቷን ቤት ያሳያት ጀመር። በዚህም እጅግ ተደነቀች። ቀጥሎም አባቷ በተሰበረ እና በሀዘን በተዋጠ መልክ ቤት ሲደርስ አየችው። እህቶቿ ያዘኑ መስለው ለመቅረብ ቢሞክሩም በእህታቸው ሞት መደሰታቸው ግን በጣም ያስታውቅባቸው ነበር።

ቀስ እያለም የመስታወቱ እይታ ጠፋ። ውቢት በዚህ ያልተጠበቀ የጭራቁ መልካምነት እና ቤተሰቧን ማየት በመቻሏ ደስታ ተሰማት።

ሊመሻሽ ሲል ውቢት ደስ የሚያሰኝ እራት ተሰርቶ አገኘች። ምንም ተጫዋቾቹን ባትመለከትም በጥሩ ጥኡመ ዜማ ስትዝናና ቆየች።

 መሽቶ እራቷን ልትበላ ስትቀመጥ የአውሬውን ድምጽ ሰምታ ከፍተኛ ድንጋጤ ዋጣት. . .

"ውቢት! እራት አብረን እንብላ?" አላት። እሷም እየተንቀጠቀጠች

"እንደፍቃድህ!" ብላ መለሰችለት።

"አይ! አንቺ የቤቱ እመቤት ነሽና መገኘቴ ከረበሸሽ ንገሪኝ እና እሄዳለሁ። ስታይኝ ፊቴ አያስጠላም?" ብሎ ጠየቃት!

"መዋሸት ስለማልፈልግ ቆንጆ ነህ አልልህም! ነገር ግን መልካምነት የተሞላህ እንደሆንክ አምናለሁ።" ብላ መለሰችለት!

"አዎን አስቀያሚ ነኝ! ከዛም በተጨማሪ ሞኛሞኝ እና ቂል ፍጥረት ነኝ።" አለ!

"እንዲህ ማሰብኮ የቂልነት ምልክት አይደለም ምክንያቱም ቂሎች እና ሞኞች እራሳቸውን እንዲህ አይረዱም!" ብላ መለሰችለት

አውሬው መመገብ እንድትጀምር ጋብዟት የሷ ደስተኝነት ምኞቱ እንደሆነ እና በዛ ግዙፍ ቤት ውስጥ የሞላው ነገር ሁሉ የሷ እንደሆነ ነገራት።

ውቢትም ከልቧ አመስግናው መልካምነቱ የመልኩን አስፈሪነት እንደደበቀው እና አሁን እንደበፊቱ አስፈሪ መስሎ እንደማይታያት ነገረችው።

"እሱስ ውስጤ መልካም ነው! ነገር ግን አሁንም ቢሆን ጭራቅ ነኝ!" ሲል መለሰላት።

"ሰዎች ሆነው እጅግ ጠያፍ እና በጭካኔ የተሞላ ስራ የሚሰሩ መልካቸው የሰው ሆኖ ስራቸው ግን የአውሬ የሆነ ከአንተ በላይ ጭራቅ ተብለው ሊጠሩ የሚገባቸው ሰዎች አሉ። ከነሱ ይልቅ አንተ በብዙ እጥፍ ትሻለኛለህ!" ብላ መለሰችለት።

ጭራቁ ቃላት ስላጠሩት "በአግባቡ አመሰግንሽ ዘንድ አቅም አጣሁ; እጅግ ከልቤ አመሰግናለሁ!" አላት።

ውቢት እራቷን ደስተኛ ሆና ከበላች በኋላ ለጭራቁም ያላት ፍርሀት ጠፍቶ ተረጋግታ ሳለ በድንገት ጭራቁ "ውቢት! ታገቢኛለሽ?" ብሎ ሲጠይቃት በድንጋጤ እራሷን ስታ ልትወድቅ ምንም አልቀራትም ነበር።

እምቢ ካልኩት ይቆጣል ብላ በመፍራት ለጥቂት ጊዜ ስታንገራግር ከቆየች በኋላ...

"አይ, አይሆንም ጭራቁ!" ብላ መለሰችለት!

ወዲያውኑ ጭራቁ መጮህ እና አስፈሪ የአውሬ ድምጽ ማሰማት ጀመረ። ድምጹም በግዙፉ ቤት ውስጥ ደጋግሞ አስተጋባ። ትንሽ ቆይቶም በሀዘን በተሞላ ድምጽ ጭራቁ "እንግዲያውስ ደህና ሁኚ ውቢት!" አለ እና ወጥቶ ሄደ።

በድጋሚ ብቻዋን ስትሆን ውቢት ለጭራቁ ከፍተኛ የሆነ ሀዘኔታ ተሰማት!

"ውይይይይ" አለች!

"እንዲህ ያለ መልካም ልብ ያለው ፍጥረት እንደዛ ያለ አስፈሪ መልክ እንዴት ይኖረዋል!? እጅግ በጣም ያሳዝናል!"

ውቢት ለሶስት ወራት በግዙፉ ቤት ውስጥ ደስተኛ ሆና ቆየች። ሁል ቀን ማታ ማታም ጭራቁ እራት ሰአት እየመጣ ይጎበኛት እና በጣም አስደሳች የሆኑ ጨዋታዎችን እየተጨዋወቱ ያመሹ ጀመር። 

ጊዜው እየገፋ በሄደ ቁጥር ውቢት በጭራቁ ውስጥ ብዙ የሚስቡ እና ደስ የሚያሰኙ ነገሮችን ማስተዋል ጀመረች።

ጉብኝቶቹንም ከመፍራት መምጫ ሰአቱን ወደ መናፈቅ እና አዘውትሮ ሳያዛንፍ የሚመጣበት ሰአት መድረሱን ለማየት ሰአቷን ደጋግማ ወደ ማየት ተሸጋገረች። ጭራቁ ሁል ጊዜ ከምሽቱ 3 ስዓት ሲል ነበር የሚመጣው።

የሚያስጨንቃት ነገር ቢኖር ሁል ጊዜ ተጨዋውተው ለእንቅልፍ ሲለያዩ ጭራቁ ሚስቱ ለመሆን ፍቃደኛ መሆኗን የሚጠይቃት ብቻ ነበር።

ከእለታት አንድ ቀን ግን ውቢት ጭንቀቷን እንዲህ ስትል ገለጸችለት

"ጭራቁ ሁል ቀን ታስጨንቀኛለህ። ላገባህ ብስማማኮ ደስ ይለኝ ነበር ግን ልዋሽህ ወይንም ላታልልህ አልፈልግም። ሁል ጊዜ እንደ ጓደኛዬ ነው የማይህ እባክህ ይህንን ለመቀበል ሞክር!" 

ጭራቁም በሀዘን ተውጦ "እድለቢስነቴን በደንብ ነው የማውቀው ቢሆንም ግን ከልቤ ነው የምወድሽ። እባክሽ መቼም ጥለሺኝ እንደማትሄጂ ቃል ግቢልኝ!" አላት።

ውቢት ግን በመስታወቱ ውስጥ የአባቷ በሷ ናፍፍቆት መታመምን አይታ ስለነበር እና እሷም በጣም ናፍቋት ስለነበር 

"መቼም ሙሉ ለሙሉ ጥዬህ ላልሄድ ቃል ልገባልህ እችላለሁ። ነገር ግን አባቴን ለማየት በጣም እፈልጋለሁ። ያንን ከከለከልከኝ ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ መውደቄ አይቀርም።" ብላ መለሰችለት!

ጭራቁም ከልቡ አዝኖላት "አንቺ ስትጨነቂ ከማይ ብሞት ይሻለኛል። በጣም ስለምወድሽ የጭንቀትሽ ምክንያት መሆን አልፈልግም። ነገ ወደ አባትሽ ልኬሽ ብቻዬን በጸጥታ እሰቃያለሁ!" አላት

በዚህ ንግግሩ በስሜት የተሞላችው ውቢት "የስቃይህ ምክንያትማ አልሆንም! በአንድ ሳምንት ውስጥ ተመልሼ ለመምጣት ቃል እገባለሁ። እህቶቼ አግብተዋል ወንድሞቼም ለውትድርና ተመልምለው ሄደዋል። አባቴ ብቻውን ስለሆነ ልሂድና ለአንድ ሳምንት አይቼው ልምጣ።" ብላ መለሰችለት

"ነገ ጠዋት ከአባትሽ ጋር ትሆኛለሽ! ቃልሽን እንዳትረሺ። ለመመለስ ስትወስኚ ይህንን ቀለበት ጠረጴዛሽ ላይ አስቀምጪና ተኚ።" ብሎ የወርቅ ቀለበት ሰጣት።

በታላቅ ሀዘን ውስጥ ሆና ውቢት ጭራቁን ተሰናበተችው። እሱም በከፍተኛ ሀዘን ተውጦ ወደመኝታው ሄደ።

በነጋታው ጠዋት ውቢት ከእንቅልፏ ስትነቃ ራሷን በአባቷ ቤት አልጋ ላይ ተኝታ አገኘች። ራስጌዋ አጠገብም ትንሽዬ ደወል አጊኝታ ብትደውላት የአባቷ ሰራተኛ በበሩ ከተፍ አለች።

ሰራተኛዋ ውቢትን ስታያት በድንጋጤ ጩኸቷን አቀለጠችው! የውቢት አባትም ጩኸቷን ሰምቶ በፍጥነት ወደክፍሉ ቢመጣ ውቢትን አያትና ከደስታው ብዛት ለሩብ ሰአት ያህል አቅፏት በደስታ ስቅስቅ ብሎ አለቀሰ።

ቀጥሎም ውቢት ከመኝታዋ ለመውጣት ፈልጋ ነገር ገን የሚለበስ ነገር የለኝም ብላ ተጨነቀች። ነገር ግን ሰራተኛዋ ከጎን ባለው ክፍል ብዙ የሚያማምሩ በወርቅ እና አልማዞች የተሽቆጠቆጡ ልብሶች የተሞሉበት ሻንጣ እንዳገኘች ነገረቻት እና ከጭንቀት ገላገለቻት። ውቢት ጭራቁን ከልቧ አመስግና ከልብሶቹ ሁሉ ከሌሎቹ አንጻር ብዙም ውበት የሌለውን መርጣ ለበሰች እና ሌሎቹን ለእህቶቿ ለመስጠት ወሰነች።

ይሄኔም ሻንጣው አነልብሶቹ ተሰወረ። የውቢት አባትም ጭራቁ ልብሶቹን ለራሷ ብቻ እንድትጠቀማቸው ማዘዙን ነገራት። ተሰውሮ የነበረው ሳጥንም ተመልሶ በአስማት ብቅ አለ። ውቢትም በጭራቁ ለጋስነት እና እንክብካቤ ውስጧ ተነካ እና በሌለበት ከልብ አመሰገነችው።

ውቢት የሚያምር ልብስ ከለበሰች በኋላ እህቶቿ ተጠርተው ከባሎቻቸው ጋር መጡ። ሁለቱም እህታቸውን ሲያዩ አልተደሰቱም ነበር። የሁለም ታላቅ የሆነችው ልጅ በጣም ውብ የሆነ ወጣት አግብታ በውበቱ ተመክቶ ሁሌ ችላ ይላት ነበር። ሁለተኛዋ እህቷ ደግሞ በጣም ቀልደኛ ነኝ ባይ እና ሁሉንም አዋራጅ አጉል ተናጋሪ ባል አግብታ ከሁሉም በላይ እያዋረዳት ነበር የምትኖረው።

ውቢትን በወርቅ እና አልማዝ ባሽቆጠቆጠ ልብስ አምራ ሲያይዋት ቅናት አቃጠላቸው። ውቢት ስለምትወዳቸው ብታቀርባቸው እና ደስታዋን ልታጋራቸው ብትሞክርም እነሱ ግን ቅናታቸውን መደበቅ አቅቷቸው ከራሳቸው ጋር ትግል ገጠሙ።

በቅናት እና ምሬት ተውጠውም የውቢት እህተቶች ወደ አትክልት ስፍራው ሄደው ስሜታቸውን እንባ እየተራጩ ማውጣት ጀመሩ።

"ይህቺ ሚጢጢ ፍጥረት ከኛ በምን ተሽላ ነው እንዲህ ደስተኛ ሆና ለመኖር የበቃችው?" እየተባባሉም እርስ በራሳቸው ተጠያየቁ!

ታላቂቱ እህትም አንድ የተንኮል ሀሳብ መጣላት። 
"ውቢትን እንደምንም ብለን ከአንድ ሳምንት በላይ እንድትቆይ እናድርጋት እና ጭራቁ ከተስማሙበት ጊዜ በላይ ስትቆይበት ተቆጥቶ ይበላታል።" አለች!

ሌላኛዋ እህትም በዚህ ተስማማች እና ውቢትን ለማታለል በመልካምነት እና በእንክብካቤ እንያዛት የሚል ሀሳብ አቀረበች።

በዚህም ተስማምተው ወደ ውቢት ተመለሱ እና በታላቅ ፍቅር እና አሳቢነት ተንከባከቧት። በዚህም ውቢት የደስታ እንባ አነባች።

ሳምንቱ እያበቃም የውቢት መመለሻ ሲቃረብ ተንኮለኞቹ እህትማማቾች በታላቅ ሀዘን ውስጥ ሆነው እያለቀሱ ውቢትን እንድትቆይ ለመኗት። በዚህም ነገር ምስኪኗ ውቢት ልቧ ስለተነካ ለተጨማሪ አንድ ሳምንት ልትቆይ ወሰነች።

ውቢት በአባቷ ቤት በቆየች ቁጥር ለምትወደው እና ለምትጨነቅለት ጭራቁ የገባችለትን ቃል መስበሯ ከፍተኛ የጥፋተኝነት ስሜት ፈጠረባት። በአስረኛው ቀን በአባቷ ቤት ተኝታ ሳለ እውን በሚመስል ህልም እራሷን በጭራቁ ግዙፍ ቤት ግቢ የአትክልት ስፍራ ጭራቁን የሞት አፋፍ ላይ ሆኖ ተኝቶ አየችው። ስትቀርበውም በተሰበረ ድምጽ ለምስጋና ቢስነቷ ሲወቅሳት ሰማችው።

ከእንቅልፏ በርግጋ ተነሳች እና ውቢት እራሷን መጠየቅ ጀመረች...

"ለጭራቁ ግን ለምንድነው እንዲህ ክፉ የሆንኩበት? በሁሉም ነገር እኔን ለማስደሰት ያልሄደበት ርቀት የለም። መልኩ እንደዛ መሆኑ የሱ ጥፋት ነው እንዴ? መልኩ ባያምርምኮ መልካምነቱ በቂ ነው። ለምን አላገባህም አልኩት? ምንአልባትኮ እህቶቼ አሁን ካላቸው የተሻለ እና ደሰትኛ ትዳር ከሱ ጋር ይኖረኝ ይሆናል። ባልኮ የሚያስደስተው መልኩ ስላማረ እና ጥበብ ስላለው ብቻ ሳይሆን ደግነት, መልካምነት እና ሰውን መረዳት የሚችል ሲሆን ነው። ይህ ሁሉ ነገር ደግሞ ጭራቁ አለው።"

ውቢት ጭራቁን ባታፈቅረውም ለሱ ትልቅ ክብር እና ቦታ እንዳላት ተገለጠላት።

"ፈጽሞ አላስከፋውም። ለሱ ምስጋና ቢስ መሆን በጣም ታላቅ ክፋት ስለሆነ መቼም እራሴን ይቅር አልልም!" አለች።

ከዛም ውቢት ጭራቁ የሰጣትን የወርቅ ቀለበት ጠረጴዛ ላይ አስቀምጣ ተመልሳ ተኛች። ወዲያውኑ እንቅልፍ ወሰዳት እና በነጋታው ጠዋት ስትነቃ ራሷን የጭራቁ ቤት ስታገኝ በታላቅ ደስታ ተሞላች።

ጭራቁን ለማየት ጓጉታ ስለነበር በጣም የሚያምር ልብስ ለብሳ መሽቶ የሚመጣበትን ሰአት በጉጉት መጠባበቅ ጀመረች። ሶስት ሰአት ሲልም የተለመደው መገናኛ ሰአታቸው ቢሆንም ጭራቁ ግን አልመጣም ነበር። ሲቆይባት ጊዜም ውቢት በጭንቀት ተውጣ ግዙፉ ቤት ውስጥ እየተዘዋወረች ፈለገችው። የትም ግን ልታገኘው አልቻለችም ነበር።

ቆም ብላ ስታስብም በህልሟ የአትክልት ስፍራው ውስጥ እንደነበረ ወድቆ ያየችው ትዝ ሲላት በጭንቀት እና በተስፋ ተውጣ እየሮጠች ወደ አትክልት ስፍራው ሮጠች።

ከአትክልት ስፍራው ስትደርስ ጭራቁን ራሱን ስቶ ወድቆ አገኘችው። እንዳየችውም ውቢት ራሷን እላዩ ላይ ወርውራ ደረቱን ማዳመጥ ጀመረች። የደከመ የልብ ምቱን ስትሰማም ከቦይ ውስጥ ውሃ በእጆቿ ጨልፋ አናቱ ላይ አፈሰሰችለት። 

ውሃው ሲያነቃው ጭራቁ ቀስ ብሎ አንኖቹን ከፈተና ውቢትን ያጣት መስሎት ታላቅ ሀዘን ውስጥ እንደገባና ምግብም መጠጥም ሳይቀምስ በታላቅ ረሀብ ከሞት አፋፍ መድረሱን ነገራት። ስላያት በጣም መደሰቱንም ነገራት።

ውቢት በስሜት ተውጣ ጭራቁን እያለቀሰች ለመነችው። እጇን ሰጥታውም ሚስቱ ለመሆን ቃል ገባችለት። ቀደም ብላ ለሱ ያላት ስሜት የጓደኝነት ብቻ እንደነበር ብታስብም የሀዘኗ ጥልቀት እሱን አጥታ መኖር እንደማትችል እንድትገነዘብ እንዳደረጋት ነገረችው። ውቢት አሁን ከጭራቁ ጋር ያላት ቀረቤታ ከጓደኝነት ያለፈ እንደሆነ ገብቷት ነበር።

ውቢት ይህንን እንደተናገረች ግዙፉ ቤት በድንገት ወሳኝ ሰአት መድረሱን በሚያመላክት አስደናቂ የብርሃን ትርኢት, የርችት ትእይንት እና ሙዚቃ ተሞላ። በዚህ ሁሉ የሚያምር ትእይንት መሀል ግን የውቢት ትኩረትም ሆነ እይታ ከተጨነቀችለት ጭራቁ ላይ ለአፍታም አልተነቀል ነበር።

አግራሞቷን ከመጠን በላይ በሚጨምር ሁኔታ ያ አስፈሪ ጭራቅ እያየችው በህይወት ዘመኗ ካየቻቸው ወጣቶች ሁሉ ውብ ወደሆነ ወጣት ሰውነት ተቀየረ። ወጣቱም ሐብዙ ዘመናት ጭራቅ አድርጎ ካኖረው እርግማን ነጻ ስለወጣችው ውቢትን ከልቡ አመሰገናት።

በወጣቱ ውበት ብትደሰትም ውቢት ግን ስለምታውቀው እና ስለወደደችው ጭራቅ ሰውዬ እጣ ፈንታ ግን ከመጠየቅ አላስቆማትም።

ወጣቱም "ይኸው ጭራቁ ከፊትሽ ተንበርክኳል። አንዲት ክፉ ጠንቋይ ልበ መልካም የሆነች ድንግል ሴት ልታገባኝ እስክትስማማ ድረስ ጭራቅ ሆኜ እንድኖር ረግማኝ ስለነበር ነው ጭራቅ ሆኜ የኖርኩት። በተጫሪም ጠንቋይዋ አሮጊት ይህንን ለማንም መናገር እንደማልችል ነበር። ከአንቺ በስተቀር ጭራቅነቴን አልፋ በመልካምነቴ ተሸንፋ ልታገባኝ የምትችል ሴት በአለም ላይ አትገኝም ነበር። በዚህም ምክንያት አንቺን በሙሉ ልቤ ላገባሽ እፈልጋለሁ።" አላት!

ውቢት በታሪኩ እየተደነቀች መልከ መልካሙን ወጣት ከተንበረከከበት እጁን ይዛ አስነሳችው። ተያይዘውም ወደ ግዙፉ ቤት ገቡ። ቤቱ ውስጥ ውቢት አባቷን እና ሌሎች ቤተሰቦቿን ስላገኘች እጅግ በጣም ተደሰተች። ለካ በዛች ውቢት በህልሟ ባየቻት ሴት አስማት አማካኝነት ወዲያውኑ ከያሉበት እንዲመጡ ተደርገው ነበር።

ሴትየዋ ውቢትን ለብልህነቷ እና ከጥበብ እና ውበት ይልቅ በጎነትን ስለመረጠች አድንቃት ሁሉንም ነገር አሟልቶ የተሰጠው ባል እንደሚገባት ተናገረች። ወጣቱ ልኡል መሆኑንም አሳውቃ አሁን ስለሚያገባ ንጉስ እንደሚሆን እና ውቢትም እጅግ የተወደደች ንግስት እንደምትሆን እምነቷን ገለጸች። 

ሴትየዋ ውቢትን ንግስናው በጎነቷን እንዳያጠፋው አደራ አለቻት።

ወደ ሁለቱ የውቢት እህቶች ዞራም ክፉ ልባቸውን ታውቅ ነበር እና የቅጣት ፍርዷን
"ሁለት ሀውልቶች ሁኑ ከእህታችሁ ቤተመንግሥት ደጃፍ ላይ ቆማችሁ ደስታዋን ትመለከቱ ዘንድ ግን ህሊና እና ልባችሁ ሁሌም ይኑር። ጥፋታችሁን አምናችሁ እስክትጸጸቱ ድረስም ይህ እርግማን አይነሳላችሁም። ኩራት, ቁጣ, ሆዳምነት, እና ስንፍና የተጸናወተው መንፈስ ሊስተካከል ይችላል። ነገር ግን ቅናተኛ እና ተንኮለኛ አእምሮ ከተስተካከለ እንደተአምር ነው የሚቆጠረው።" አለቻቸው

በአስማትም ሴትየዋ በቅጽበት ሁሉንም ሰው ወደ ቤተመንግሥት ወሰደች። የልኡሉ አገልጋዮችም በታላቅ ደስታ እና ድግስ ተቀበሏቸው። 

ከዛም ልኡሉ ውቢትን አግብቶ ለብዙ አመታት በደስታ እና በደግነት ብዙ ልጆች ወልደው ኖሩ!

ተጨማሪ አዳዲስ ታሪኮች

አእምሮና ምናገባህ: Amharic tales for Children

ምናገባህ እና አእምሮ

ጥጃው ሳምሶን: Amahric story for children

ጥጃው ሳምሶን

የስሜት ህዋሳት ጸብ: Amharic tale

የስሜት ህዋሳት ጸብ

Ethiopian National Flag

የኢትዮጵያ ህዝቦች ብሄራዊ መዝሙር

Teaching about maps

ካርታ ምንድነው?

Water cycle (የውሃ ኡደት)

የውሃ ኡደት (Water cycle)

ሰባተኛው እና የመጨረሻው የሲንባድ ጉዞ: Amharic tales

ሰባተኛው እና የመጨረሻው የሲንባድ ጉዞ

ስድስተኛው የሲንባድ ጉዞ: Amharic tales

ስድስተኛው የሲንባድ ጉዞ

search

ተረት መፈለግያ