ካርታ ምንድነው?
እንዴት ቆያችሁኝ ልጆችዬ?
ዛሬ ስለ ካርታ ምንነት እና በውስጡ ምን ምን እንደሚያካትት, እንዴት ካርታ ልንስል እና ልናነብ እንደምንችል እንማማራለን እሺ!
በመጀመርያ ካርታ ምን እንደሆነ በማብራራት እንጀምር!
ካርታ ማለት የመሬትን ገጽታ ሙሉ ለሙሉ ወይንም
በከፊል በዝርግ ወይንም ጠፍጣፋ አካል ላይ በተሳለ ስእል የሚያሳይ መግለጫ ነው።
በዚህ ማብራሪያ ውስጥ ዝርግ ወይንም ጠፍጣፋ የምንለው አካል ወረቀት, የኮምፒውተር ወይንም የስልክ ስክሪን ሊሆን ይችላል።
ካርታን ተጠቅመን የተለያዩ በምድር ላይ የሚገኙ ነገሮችን መገኛ ቦታ ማወቅ እና መጠቆም እንችላለን።
ካርታን ለማዘጋጀት ከእርሳስ እና ማስመርያ ጀምሮ ምድርን እየዞሩ ፎቶ እስከሚያነሱ ሰው ሰራሽ ሳተላይቶች የሚደርሱ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን እና የተለያዩ መሳርያዎችን እንጠቀማለን።
ካርታ የማዘጋጀት ሙያ Cartography (ካርቶግራፊ) ተብሎ ሲጠራ ካርታን የሚያዘጋጅ ባለሙያ ደግሞ Cartographer (ካርቶግራፈር) ተብሎ ይጠራል።
ስለዚህ ካርታ ማለት በመሬት ላይ የሚገኙ አካላትን ማለትም ዛፎችን, ወንዞችን, ገደሎችን, ተራራና አቀበቶችን, ህንጻዎችን, ድልድዮችን እና ሌላም ሌላም ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሮአዊ አካላትን በጠፍጣፋ አካል ላይ በመሳል ለማሳየት የሚጠቅም የመረጃ ቴክኖሎጂ ነው።
አቅጣጫ ምንድነው?
አንድ የሚንቀሳቀስ ነገር ምንጊዜም ቢሆን አቅጣጫ ይኖረዋል። ግን አቅጣጫ ምንድነው?
ለምሳሌ አንድ ክፍል ውስጥ መሀል ላይ ቆማችኋል እንበል! ከዛ ከቆማቹበት ቦታ ተነስታችሁ ወደሆነ ሌላ ቦታ ለመሄድ ብትፈልጉ ወዴት በኩል መሄድ እንዳለባችሁ ማወቅ ይኖርባችኋል! አቅጣጫ ማለት ያ ነው። ወደምትፈልጉበት ቦታ ለመሄድ የምትጓዙበት መስመር ነው አቅጣጫ ማለት።
በእለት ተእለት ኑሮአችን የምንጠቀማቸው አራት ዋና ዋና አቅጣጫዎች አሉ! እነሱም ወደላይ, ወደታች ወደግራ, እና ወደቀኝ ናቸው።
ወደ ካርታ ስንመጣ ግን የምንጠቀማቸው ዋና ዋና (አበይት) አቅጣጫዎች የተለዩ ናቸው።
የካርታ አበይት አቅጣጫዎች:
አንድ ሰው ፊቱን ወደ ጸሃይ መውጫ ማለትም ወደ ምስራቅ አዙሮ ቢቆም፣ በስተግራው ሰሜን፣ በስተቀኙ ደቡብ በስተኋላው
ደግሞ ምዕራብ አቅጣጫዎች ይገኛሉ፡፡

የካርታን አቅጣጫ ማንበብ
ቀደም ሲል እንደተመለከትነው ካርታ በምድር ላይ የሚገኙ የተለያዩ ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ አካላትን መጠነ ስፋት እና መገኛ ቦታ ለማወቅ ይረዳል።
ነገር ግን ይህንን የካርታ ጥቅም ለማግኘት በመጀመሪያ የካርታ ንባብ ክህሎታችንን ልናዳብር ይገባናል።
የካርታ አቅጣጫ ማለት በካርታው ላይ ያለው የመሬት
ስእል መሬት ላይ ካለው አቅጣጫ ጋር ተስተካክሎ እንዲቀመጥልን እና ካርታውን ስናነብ በቀላሉ ለማመሳከር እንዲመቸን ተብሎ በካርታው
ላይ የሚቀመጥ አቅጣጫ ጠቋሚ ቀስት ነው።
የካርታ አቅጣጫ አብዛኛውን ጊዜ ወደ ሰሜን አቅጣጫ ነው የሚጠቁመው።
አንጻራዊ መገኛ (Relative location)
አንጻራዊ መገኛ ማለት የአንድን ነገር መገኛ
በአካባቢው ከሚገኙ ሌሎች ነገሮች ጋር አነጻጽሮ በመግለጽ የሚያመለክት ነው።
ለምሳሌ:
- ከኢትዮጵያ በስተደቡብ ኬንያ ትገኛለች።
- ከአዲስአበባ በስተሰሜን አቅጣጫ 500 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ባህርዳር ከተማ ትገኛለች።
- ከትምህርት ቤታችን ፊትለፊት ቤተመጻሕፍት አለ።
- የሰሃራ በረሀ ከአትላንቲክ ውቅያኖስ በስተምስራቅ ከቀይ ባህር ደግሞ በስተምእራብ ይገኛል
ከላይ የተመለከትናቸው አረፍተነገሮች አንጻራዊ መገኛ በመጠቀም የአንድን ነገር መገኛ የሚያመለክቱ ናቸው።
በመጀመርያው ምሳሌ ከኢትዮጵያ አንጻር ኬንያ የት እንደምትገኝ ያመለከትን ሲሆኑ በሌሎቹ ምሳሌዎችም ተመሳሳይ ነገርን እንመለአታለን።
አንጻራዊ መገኛን መጠቀም እጅግ በጣም ቀላል ሲሆን ይህንን ለመጠቀም ማነጻጸርያ ነጥቦች አስፈላጊ ናቸው።
አንጻራዊ
መገኛ የአገርን፣ የክልልን ወይም የአህጉርን መገኛ ከየብስ፣ ከውሃ አካላት
ወይም ከአጎራባች አገሮች ጋር በማነፃፀር ይገልፃል፡፡
በከተሞች አካባቢ ደግሞ ትላልቅ ሕንፃዎችን፣ መንገዶችን፣ ድልድዮችን
በማነፃጸሪያነት መጠቀም እንችላለን፡፡
አንጻራዊ መገኛን ለመግለፅ የአካባቢ
ታዋቂ ቦታዎችን ስም እና ዓራቱ
መሠረታዊ አቅጣጫዎችን (ሰሜን፣
ደቡብ፣ ምሥራቅ እና ምዕራብ)
መጠቀም አስፈላጊ ነው፡፡
የሚከተለው ሰንጠረዥ የኢትዮጵያ አንጻራዊ መገኛን ከተለያዩ ጎረቤት ሀገራት አንጻር ያሳየናል
እስኪ የሚከተለውን የምስራቅ አፍሪካ ሃገራት
የሚያሳይ ካርታ ተመልክታችሁ የተለያዩ ሀገሮች ያላቸውን አንጻራዊ መገኛ ለመናገር ሞክሩ!

ፍጹማዊ መገኛ (Absolute location)
ፍጹማዊ መገኛ ምን እንደሆነ ከማብራራታችን በፊት እስኪ እሱን በቀላሉ እንድትረዱ የሚያደርጓችሁን ነገሮች ተራ በተራ እንመልከት:
ባለ አራት ወይንም ባለ ስድስት ፍርግርግ የማጣቀሻ ሥርዓት (The four/six Grid System)
በካርታ ላይ የአንድ ቦታን በፍጹማዊ መገኛ ለማሳየት ፍርግርግ የማጣቀሻ ሥርዓትን እንጠቀማለን፡፡ ፍርግርግ የማጣቀሻ ሥርዓት ወደላይ እና ወደጎን ቀጥ ብለው በመሰመር ብዙ አራት ማእዘኖችን የሚሰሩ መስመሮችን የራሳቸው የሆነ መለያ ኮድ በመስጠት የአንድን ቦታ መገኛ የምንጠቁምበት ስርአት ነው፡፡ ለምሳሌ የሚከተለውን ምስል እንመልከት:

በምስሉ ላይ የቀዩን ቦታ መገኛ በባለአራት አሃዝ ፍርግርግ ስርዓት ለመጠቆም በመጀመርያ ቀጥ ብለው የቆሙትን መስመሮች መለያ ቁጥር ቀዩ አራት ማእዘን
እስካለበት የመጀመርያ መስመር ድረስ ከግራ ወደቀኝ አንቆጥራለን፡፡ ቀጥለን ደግሞ ከታች ወደላይ በተመሣሣይ ሁኔታ ወደጎን የተኙትን መስመሮች በመቁጠር ልክ
ቀዩን አራት ማእዘን ያለበት ስንደርስ እናቆማለን፡፡ በዚህም መሰረት የቀዩን ቦታ መገኛ በአራት አሃዝ ፍርግርግ ስርዓት ስንገልጽ 15, 23 ይሆናል ማለት ነው፡፡
በተመሳሳይ መንገድ የቢጫው 16, 25 ሲሆን የአረንጓዴው ደግሞ 18, 22 ይሆናል ማለት ነው፡፡
እስኪ በካርታው ላይ ያሉ ሌሎች አራት
መእዘን ቦታዎችን እየለያችሁ በባለአራት አሃዝ ፍርግርግ ስርዓት መገኛቸውን ለመጠቆም ሞክሩ!!
እንደተመለከትነው ባለ አራት አሃዝ ፍርግርግ ስርአት በጣም ሰፊ ቦታን አካልሎ ሲሆን የሚጠቁመው አነስ ያሉ ቦታዎችን ለማግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡ ስለዚህም ይህንን ችግር ለመፍታት እና ቦታዎችን በተሻለ ትክክለኛነት ለመጠቆም ባለ ስድስት አሃዝ ፍርግርግ ስርአትን እንጠቀማለን ማለት ነው፡፡
ባለ ስድስት አሃዝ ፍርግርግ ስርአትን ለመጠቀም በባለ አራት አሃዝ ስርአትን ተጠቅመን የቦታውን መገኛ ካወቅን በኋላ የበለጠ ቦታዉን አቅርበን በማየት ዉስጡ ከ1 ጀምሮ አስከ ዘጠኝ የሚቆጥሩ ሌሎች ፍርግርጎችን አጊኝተን እንቆጥረለን መለት ነው፡፡ ይሄም በተሻለ ቀረቤታ ቦታዉን እንድንገልጽ ስለሚረዳን ትክክለኛነቱን በጣም የተሻለ ያደርገዋል ማለት ነው፡፡
ለምሳሌ ከቅድሙ ምሳሌ በቀዩ ቦታ ዉጥ የሚገኝ ቦታን በተሻለ ትክክለኛነት ባለ ስድስት አሃዝ ፍርግርግ ስርአትን ተጠቅመን
ለማሳየት ብንፈልግ የሚከተለውን እናገኛለን፡

በምስሉ ላይ የነጥብ “A”ን መገኛ በባለ ስድስት አሃዝ ፍርግርግ ስርአት መጠቆም ብንፈልግ 153, 235 ይሆናል ማለት ነው፡፡ በተመሳሳይም የነጥብ B 158, 231 እና የነጥብ C ደግሞ 158, 238 ይሆናል ማለት ነው፡፡
1. ኬንትሮስ (Longitude)፡
በካርታ ላይ ከሰሜን ወደ ደቡብ፣ ማለትም ከላይ ወደታች የተሰመሩ መስመሮች ሲሆኑ ጥቅማቸው ግን አንድ በምድር ላይ ያለ አካል ወደ ምስራቅ ወይንም ወደ ምዕራብ አቅጣጫ ያለበትን ቦታ በትክክል ለመጠቆም ነው፡፡
የኬንትሮስ መስመሮች በብዛት 360 ናቸው፡፡ አነዚህ መስመሮች በሉል (Globe) ላይ ሲሳሉ ሰሜን እና ደቡብ ዋልታዎች ላይ ይገናኛሉ፡፡
በኬንትሮስ መስመሮች መካከል ያለው ርቀት የሚለካው በዲግሪ ነው፡፡
የኬንትሮስ መስመሮች ሲሳሉ ከላይ ወደ ታች ስለሆነ
ሌላኛው መጠሪያቸው "ቋሚ-መስመሮች" የሚል ነው፡፡
ኬክሮስ (Latitude)፡
በካርታ ላይ አግድም፣ ማለትም ከምስራቅ ወደ ምእራብ የተሰመሩ መስመሮች ሲሆኑ በምድር ላይ ያሉ አካላት ወደ ሰሜን ወይንም ደቡብ አቅጣጫ ያሉበትን ቦታ በትክክል ለመጠቆም ይረዳሉ፡፡
የኬክሮስ መስመሮች በብዛት 180 ናቸው፡፡ እነዚህ መስመሮች ፈጽሞ የማይተላለፉ ተይዩ መስመሮች ናቸው፡፡
የኬክሮስ መስመሮች ሲሳሉ ወደ ጎን ተጋድመው
ስለሆነ ሌላኛወ መጠሪያቸው አግድም-መስመሮች የሚል ነው፡፡
አብይ ቋሚ መስመር (Prime Meridian or Greenwich Meridian)፡
ይህ የኬንትሮስ መስመሮች ሲቆጠሩ ከሁሉም ቀድሞ የሚቆጠረው ሲሆን ልኬቱ ደግሞ 0 ዲግሪ ነው፡፡ ይህ ምናባዊ መስመር ምስራቃዊ ንፍቀ ክበብ እና ምዕራባዊ ንፍቀ ክበብ (Eastern Hemisphere and Western Hemisphere) ብለን ምድራችንን እንድንከፋፍል ረድቶናል፡፡
ይህም ማለት፣ ከዚህ መስመር ተነስተን ነው ካርታ ስናነብ አንድ በምድር ላይ ያለ አካል ወደ መስራቅ ወይንም ወደ መእራብ ያለውን ርቀት የምንለካው፡፡ አብይ ቋሚ መስመር ስምንት ሀገራትን አቋርጦ ሲሆን የተሰመረው እነሱም፡ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ እና ስፔን በአውሮፓ፣ እንዲሁም አልጄሪያ፣ ማሊ፣ ቡርኪናፋሶ፣ ቶጎ እና ጋና በአፍሪካ ነቸው። አብይ ቋሚ መስመር በሌላ ስሙ ትልቁ ሜሪዲያን ተብሎም ይጠራል፡፡
የምድር ወገብ መስመር (Equator)፡
ይህ የኬክሮስ መስመሮች መነሻ ሲሆን ልኬቱም 0 ዲግሪ ነው፡፡ የምድር ወገብ መስመር ምድራችንን ወደ ጎን እኩል ቆርጦ በመክፈል ካላይኛውን ክፍል ሰሜናዊ ንፍቀ ክበብ (Northern Hemisphere)፣ ታችኛውን ክፍል ደግሞ ደቡባዊ ንፍቀ ክበብ (Southern Hemisphere) ብለን እንድንጠራ አስችሎናል፡፡
የምድር ወገብ መስመር በ13 ሀገራት ያልፋል፣ እነሱም፡ ኢኳዶር ፣ ኮሎምቢያ ፣ ብራዚል ፣ ሳኦቶሜ እና ፕሪንሲፔ ፣ ጋቦን ፣ ኮንጎ ሪፐብሊክ ፣ ኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ፣ ኡጋንዳ ፣ ኬንያ ፣ ሶማሊያ ፣ ማልዲቭስ ፣ ኢንዶኔዥያ እና ኪሪባቲ ናቸው።
እነዚህን ሃሳቦች በደንብ ከተረዳን ፍጹማዊ መገኛን
በቀላሉ መረዳት ስለምንችል ቀጥሎ እሱን ወደ ማብራራት እንሂድ፡:
ፍፁማዊ መገኛ በምድር ገጽ ላይ የአንድን ቦታ
ወይም ነገር ትክክለኛ መገኛን ኬክሮስ እና ኬንትሮስን በመጠቀም ያሳያል፡፡ ኬክሮስ አንድ ቦታ በሰሜን ወይም በደቡብ አቅጣጫ ከምድር
ወገብ መስመር ምን ያህል እንደሚርቅ ይገልጻል፣ ኬንትሮስ ደግሞ አንድ ቦታ በምስራቅ ወይም በምዕራብ አቅጣጫ ምን ያህል ከአብይ
ቋሚ መስመር እንደሚርቅ ያሳያል።
ለምሳሌ የአዲስ አበባ ፍጹማዊ መገኛ 9° 1′ 48″ ሰሜን, 38° 44′ 24″ ምስራቅ ነው፡፡ ይህም ሲተነተን፡
- 9° 1′ 48″ ሰሜን የሚለው የኬክሮስ ልኬት ማሳያ ሲሆን፣ አዲስ አበባ ከምድር ወገብ መስመር
(Equator) ምን ያህል ርቃ በስተ ሰሜን እንደምትገኝ ያሳያል፡፡
- 38° 44′ 24″ ምስራቅ የሚለው ደግሞ የኬንትሮስ ልኬት ማሳያ ሲሆን፤ አዲስ አበባ ከአብይ ቋሚ መስመር
(Prime Meridian) ምን ያህል ርቃ በስተምስራቅ እንደምትገኝ ያሳያል፡፡
እነዚህ ሁለት መስመሮች የሚገናኙበት ቦታ፣ ማለትም, 9° 1′ 48″ ሰሜን, 38° 44′ 24″ ምስራቅ የአዲስ አበባ ፈጹማዊ መገኛ ነው ማለት ነው፡፡
የምድር ዋና ዋና የኬክሮስ መስመሮች
ቀደም ብለን እንደተማማርነው የኬክሮስ መስመሮች በብዛት 180 ሲሆኑ ምድራችንን መሃል ለመሃል እኩል ለሁለት የሚከፍላት የኬክሮስ መስመር “የምድር ወገብ መስመር” (Equator) ይባላል፡፡ የላይኛው ግማሽ የሰሜን ንፍቀ ክበብ ሲሆን 90 የኬክሮስ መስመሮች አሉት፡፡ የታችኛው ደግሞ የደቡብ ንፍቀ ክበብ ሲሆን እሱም በተመሳሳይ 90 የኬክሮስ መስመሮች አሉት፡፡ በድምሩ 180 የኬክሮስ መስመሮች አሉ ማለት ነው፡፡
የምድር ወገብ አንድ እራሱን የቻለ ንፍቀ ክበብ ሲሆን ደቡብ እና ሰሜን ንፍቀ ክበቦች እራሳቸውን ችለው በሌሎች ሁለት ሁለት ዋና ዋና የኬክሮስ መስመሮች ይከፋፈሉና ምድርን በአጠቃላይ ለአምስት የተለያዩ ክፍሎች ይቆርሷታል፡፡
እስኪ እነዚህን ክፍሎች ለየብቻ እንመልከት:

- የካንሰር ሞቃታማ የሃሩር መስመር (Tropic of Cancer )፡
ይህ መስመር ከምድር ወገብ ወደላይ፣ ማለትም ወደ ሰሜን 23.50 ከፍ ብሎ የሚገኝ የኬክሮስ መስመር ነው፡፡ በሰሜናዊው ንፍቀ ክበብ በበጋው ወቅት እኩለ ቀን ላይ ፀሐይ በቀጥታ ከኣነት በላይ ሆና የምትታይበትን ሰሜናዊ ጫፍ ያመለክታል።- የካፕሪኮርን ሞቃታማ የሃሩር መስመር (Tropic of Capricorn)፡
ይህ መስመር ከምድር ወገብ ወደታች፣ ማለትም ወደ ደቡብ 23.50 ዝቅ ብሎ የሚገኝ የኬክሮስ መስመር ነው፡፡ ይህ ምናባዊ መስመር በደቡባዊው ንፍቀ ክበብ በበጋው ወቅት እኩለ ቀን ላይ ፀሐይ በቀጥታ ከአናት በላይ ሆና ወደ ላይ የምታበራበትን ደቡባዊ ጫፍ ያመለክታል።ይህ በ00 ኬክሮስ ላይ የሚገኝ ሲሆን ምድርን ወደ ሰሜናዊ ንፍቀ ክበብ እና ደቡባዊ ንፍቀ ክበብ ለመከፋፈል እንደ መካከለኛ መስመር ያገለግላል።
- የአርክቲክ ክበብ (Arctic Circle)፡
ይህ 66.5 ዲግሪ ኬክሮስ ላይ የሚገኝ መስመር ነው፡፡ የአርክቲክ ክበብ የአርክቲክ ክልልን የሚወስን ጉልህ መስመር ሲሆን ፀሀይ ከአድማስ በላይ ለ24 ተከታታይ ሰአታት የምትቆይበትን ደቡባዊ ጫፍ ያሳያል።- አንታርክቲክ ክበብ (Antarctic Circle)፡
በ66.5 ዲግሪ ደቡብ ኬክሮስ የሚገኘው የአንታርክቲክ ክበብ በደቡባዊ ንፍቀ ክበብ በበጋው ክረምት ፀሐይ ከአድማስ በላይ ሆና ቀን ሙሉ የምትቆይበትን ሰሜናዊ ጫፍ ያመለክታል። ይህ ኬክሮስ የአንታርክቲክ ክልልን ይከብባል።ካርታን በዲጂታል በቴክኖሎጂ
በዲጂታል አለም ካርታዎች እንደ ምትሃታዊ መስኮቶች በምድር ላይ ያለን ማንኛውም ቦታ ሊያሳዩ የሚችሉ እጅግ በጣም ጠቃሚ እና ምቹ ቴክኖሎጂዎች ናቸው! እነዚህ ዲጂታል ካርታዎች እንደ ስልኮች፣ ታብሌቶች እና ኮምፒተሮች ባሉ መሳሪያዎች ላይ ሊጠቀሙ የሚችሏቸው እጅግ በጣም ጥሩ የወረቀት ምትክ ስሪቶች ናቸው።
አንድ ትልቅ የወረቀት ካርታ ከመዘርጋት ይልቅ፣ የስልክ እስክሪንን ነካ ነካ በማድረግ ብቻ በአለም ላይ ያሉ ማንኛውም መንገዶችን፣ ህንፃዎችን፣ መናፈሻዎችን እና ውቅያኖሶችን በሚያስደንቅ ሁኔታ ማየት ይቻላል።
ዲጂታል ካርታዎች እየተራመዱ፣ መኪና እያሽከረከሩ ወይም በሕዝብ ማመላለሻ እየተጓጓዙ፣ ከአንዱ ቦታ ወደ ሌላ ለመንቀሳቀስ ምርጥ መንገደረ በመምረጥም ያግዛል።
ስለዚህ፣ ልክ እንደ አስማት፣ ዲጂታል ካርታዎች መላውን ዓለም በቀጥታ ወደ የሰው ልጅ መዳፍ ላይ ያመጣሉ ማለት ነው፡፡
እስኪ እነዚህነ ዲጂታል የካርታ ቴክኖሎጂዎች እንመልከት:
GPS (Global Positioning System):
በመሬት ዙሪያ የሚሽከረከሩ ሰው ሠራሽ ሳተላይቶችን በመጠቀም የተለያዩ መረጃዎችን ወደ መሬት የሚያቀብሉ መተግሪያዎች ወይም መሳሪያዎች (devices) ናቸው፡፡
የጂፒኤስ መሣሪያዎች አቅጣጫን ያሳያሉ፡፡ በተጨማሪም በየብስ፣ በመኪናና በአየር ላይ የሚንቀሳቀሱ አካላትን አቅጣጫ ለመጠቆም እንዲሁም ፍጥነታቸውን ለመቆጣጠር ያግዛሉ፡፡
ጎግል ካርታ (Google Maps):
ጎግል ካርታ በቀጥታ ከጎግል በመሬት ላይ የምንፈልገውን አካባቢ ካርታ በተንቀሳቃሽ ስልክ (በሞባይል) ወይም በኮምፒውተር አማካኝነት አንድን ቦታ በቀጥታ ለማመልከት የሚያስችል መተግበሪያ ነው፡፡ ለምሳሌ
ከታች የተቀመጠው ጎግል ካርታ በኢትዮጵያ ድንቅ እና ዉድ የሆነውን የጎንደር ፋሲል ግቢ መገኛ ያሳያል፡፡
ይህ መተግበሪያ የአንድ ቦታን አቅጣጫ፣ የአካባቢን የገበያ ትስስር እና የመሳሰሉትን ለመፈለግ ይጠቅማል፡፡ ስለዚህም ሰዎች በቀላሉ ወደ ማያውቁት ቦታ ለመሄድ፣ መልዕክት ለማድረስ፣ ሰዎችን በቀላሉ ለማግኘት ሲፈልጉ የጎግል ካርታ መፈለግያን መጠቀም ይቻላል፡፡
ጎግል ኧርዝ (Google Earth):
በሕዋ ላይ በተቀመጡና በመሬት ዙሪያ በሚሽከረከሩ ሰው ሰራሽ ሳተላይቶች አማካኝነት የመሬትን ትክክለኛ ገጽታ ለማሳየት የሚገለግል መተግበሪያ ነው፡፡
ተመራማሪዎች ጎግል ኧርዝን በመጠቀም ሩቅ ያሉ ቦታዎችን ለማየት እና ለመመርመር፣ ስለተለያዩ በሽታዎች መከሰት ትንበያ ለመስጠት እንዲሁም የተፈጥሮ ሀብቶችን ለመፈለግ፣ ለማየት እና ለመንከባከብ የሚያስችል ተግባራትን ያከናውናል፡፡